የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ከግምት በማስገባት የከተማውን የአገልግሎት ሁኔታ ለማሻሻል ሲባል በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ምክንያት መታወቂያቸውን ማደስ ሲኖርባቸው ያላደሱ ነዋሪዎች በመታወቂያቸው አገልግሎት ማግኘት እንዲችሉ መደረጉን በኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ በተለይ ለብሰራት ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡
የነዋሪነት አገልገሎት፣መሸኛ፣መታወቂያ ማደስ ፣በጠፋ ምትክ መውሰድ አገልግሎት በመቆሙ የተነሳ ተገልጋዮች ቅሬታ ማቅረባቸውን ተከትሎ ፍቃዱ ሊሰጥ መቻሉን አንስተዋል፡፡
ከተከለከሉ የአገልግሎት አይነቶች ውጪ በ2014 ዓ.ም መታወቂያቸውን ማደስ ሲኖርባቸው ያላደሱ ነዋሪዎች ከታህሳስ 21 ቀን2014ዓ.ም ጀምሮ በነዋሪነት ቅፅ ላይ መኖራቸው ተመሳክሮ እና በቅፅ 02 የግል መረጃቸውን አለመቀየራቸው ተረጋግጦ በተቋሙ የሚሰጡ አገልግሎቶችን እንዲያገኙ ተፈቅዷል፡፡
በዚህም መሰረት የልደት፣የጋብቻ ፣የሞት እና መሰል የምስክር ወረቀት አገልገሎትን ነዋሪዎች ማግኘት ይችላሉ፡፡
በቤተልሄም እሸቱ