
በ2012 ዓ.ም መስከረም ወር ላይ የግንባታ ስራው የተጀመረው የአውቶቢስ ተራ-መሳለሚያ-18 ቁጥር ማዞሪያ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በታቀደለት ጊዜ አለመጠናቀቁ በነዋሪዎች ዘንድ ቅሬታ ማስነሳቱን ብስራት ሬዲዮ ሰምቷል፡፡
የመንገድ ፕሮጀክቱ በሁለት ዓመት የጊዜ ገደብ ውስጥ መጠናቀቅ የነበረበት ሲሆን በወሰን ማስከበር ችግር ምክንያት አለመጠናቀቁ ተገልፆል፡፡መንገዱን 3.4ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን በ40 ሜትር የጎን ስፋት እየተገነባ ይገኛል፡፡
እስካሁን ድረስ ባለው አጠቃላይ ሂደት ከአውቶብስ ተራ ጀምሮ ወደ መሳለሚያ አቅጣጫ 700 ሜትር የሚሆነው የመንገዱ ክፍል ግራ እና ቀኝ የመጀመሪያ ደረጃ አስፓልት የማንጠፍ ስራ ተከናውኗል፡፡
ነገር ግን ከመሳለሚያ ወደ 18 ቁጥር ማዞሪያ ያለው መንገድ በወሰን ማስከበር ችግር ምክንያት የግንባታ እንቅስቃሴው በሚፈለግ ደረጃ እየተከናወነ አለመሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ እያሱ ሰለሞን ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡
ከመሳለሚያ ወደ 18 ቁጥር ማዞሪያ ያለው የመንገድ ፕሮጀክት 11.2 በመቶ ብቻ አፈፃፀም ላይ የሚገኝ ሲሆን ግንባታውን ለማፋጠን በአሁኑ ወቅት መነሳት ያለባቸው ህገ ወጥ ቤቶች እየተነሱ ይገኛል፡፡የመንገድ ፕሮጀክቱ በቻይና ሬል ዌ ሰቨንስ ግሩፕ በሚባል የስራ ተቆራጭ እየተገነባ ያለ ሲሆን ይህው ፕሮጀክት 1.2 ቢሊየን ብር በላይ በመሆነ ወጪ እየተገነባ ይገኛል፡፡
በሳምራዊት ስዩም