መደበኛ ያልሆነ

ጥር 6፤2014-የግብፅ ፕሬዝዳንት የሱዳን መፈንቅለ መንግስትን ደግፈዋል መባላቸዉን አስተባበሉ

የግብፅ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ጎረቤት ሀገር በሆነችዉ ሱዳን በተፈጸመዉ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት እና የሲቪል አገዛዝ እንዲቀጥል በሚደረገዉ ተቃዉሞ ዙሪያ ዝምታቸውን ሰብረዋል፡፡ግብፅ ከሱዳን የጦር ሃይል መሪ አብደል ፋታህ አል ቡርሃን ጋር ወግናለች የሚል ክስ በተደጋጋሚ የሚቀርብባት ሲሆን ፕሬዝዳንት አል ሲሲ ግን ክሱን አጣጥለዉታል፡፡

በሻርም ኤል ሼክ እየተካሄደ ባለው የአለም ወጣቶች ፎረም ላይ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ የሰጡት ፕሬዝዳንቱ “ምንም ዓይነት ይፋዊ መግለጫ ስላላወጣን ወደ አንዱ ወይም ወደ ሌላኛዉ ወገን ተሰልፈናል ማለት አይደለም” ሲሉ ተናግረዋል።የሱዳን የፖለቲካ ቀውስ እንዲያበቃ ወታደራዊ አገዛዝም ሆነ ተቃዋሚ ሀይሎች ውይይት እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተናጥል በግብፅ፣ ኢትዮጵያ እና ሱዳን መካከል በታላቁ የኢትዮጲያ የህዳሴ ግድብ ላይ የተካሄደው ድርድር መቋረጥ እንዳሳዘናቸውና ይህም በሀገራቱ መካከል ለአስር አመታት የዘለቀው አለመግባባት መንስኤ መሆኑን ተናግረዋል።

የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት የህዳሴው ግድብ ጉዳይ በአፍሪካ ህብረት መፈታት ያለበት ጉዳይ ነው ካለ ወራትን ቢያስቆጥርም ግብጽ እና ሱዳን አቋማቸውን እና ፍላጎታቸውን ስለሚቀያይሩ እንጂ ኢትዮጵያ ሁሌም ዝግጁ ናት ሲሉ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ መናገራቸዉ ይታወሳል፡፡

በሚኪያስ ጸጋዬ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *