
በኢትዮጵያ እያደገ የመጣዉን የኦንላይን ግብይትን የሚያጠናክር ሻጭን ከገዢ በቀጥታ የሚያገናኝ ድረገጽ በኢትዮ ማርክ አማካይነት በዛሬው እለት ይፋ ተደርጓል።
ድረገጹ በሻጭና በገዢ መካከል የሚገቡ ደላሎችን ለማስቀረት አልሞ የተመሰረተ መሆኑን የኢትዮ ማርክ ማርኬቲንግ እና የኮሚኒኬሽን ባለሙያ ኢንጂነር ነጂላ መሀመድ በማስጀመሪያ ስነስርዓቱ ላይ ተናግረዋል።
የኢትዮ ማርክ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ፋሪስ አወል በበኩላቸው ሻጩ ለመሸጥ የፈለገውን ንብረት በቀጥታ በድረገጹ ላይ ያለ ክፍያ በመለጠፍ ገዢን በቀላሉ ለማግኘት የሚያስችል በመሆኑ ለየት ያደርገዋል ብለዋል።
በተጨማሪም ድረገጹ የዋጋ ንረትን ለመከላከል ሻጮች የተጋነነን ዋጋ ለንብረታቸው እንዳይሰጡ በገጹ ላይ ከመለጠፉ በፊት ማጣራቶችን እንደሚያደርግም ተነግሯል።
ድረ ገጹ ሰዎች መግዛት የሚፈልጓቸዉን እቃዎች ካለድካም እንዲያገኙ እንዲሁም ሰፊ ምርጫን ለሸማቹ የያዘ በመሆኑ ለየት ያደርገዋል ተብሏል።
በበረከት ሞገስ