መደበኛ ያልሆነ

ጥር 13፤2014-በአዲስ አበባ በትላንትናው እለት የደረሰውን የእሳት አደጋ ለመቆጣጠር ስምንት ሰዓት ወስዷል❗️

በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ልዩ ቦታው አትላስ አካባቢ የቅዱስ ኡራኤል ቤተክርስቲያን በሆነው የግንባታ እና የባኞቤት እቃዎች መጋዘን ላይ በደረሰው የእሳት አደጋ 2.5 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ወድሟል።እሳቱን ለማጥፋት በተደረገው ጥረት 50 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት ማዳን መቻሉን የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።

የኮሚሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ የእሳት አደጋውን አስመልክቶ ለብስራት ሬድዮ በሰጡት ማብራሪያ እሳቱ ከቀኑ 7:30 መከሰቱ መረጃ እንደደረሳቸው እና ባለሙያዎቹ በስፍራው መደረሳቸውን ተናግረዋል።

አደጋው ሙሉ በሙሉ እንዲጠፋ በተደረገው ጥረት ከቀኑ አስራ አንድ ሰዓት ለመቆጣጠር የተቻለ ሲሆን በሰው ላይ የደረሰ ምንም ጉዳት እንደሌለም ገልፀዋል። የእሳት አደጋውን ለማጥፋት 14 የእሳት አደጋ መቆጣጠር ተሽከርካሪዎች እና ሁለት አምቡላንስ ቦታው ላይ ተሰማርተዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ አንድ የእሳት አደጋ መቆጣጠር ተሽከርካሪ እንዲሁም የአዲስ አበባ ውሃ ባለስልጣን አንድ ውኃ የጫነ ቦቴ በመላክ አደጋውን ለመከላከል አግዘዋል።

እሳቱ ለግንባታ አገልግሎት የሚውሉ የመታጠቢያ ቤት፣ የሕንፃ መሣሪያ እቃዎችንና መሰለ የግንባታ ቁሳቁሶችን የያዙ ፈጣን ተቀጣጣይ እቃዎች መሸጫ መጋዘኖች ላይ በመድረሱ በፍጥነት ለመቆጣጠር አስቸጋሪ ማድረጉንም ባለሙያው ተናግረዋል።

እሳቱ 400 ካሬ የሸፈነ ሲሆን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር ስምንት ሰዓት መፍጀቱን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

በትግስት ላቀው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *