መደበኛ ያልሆነ

በኢትዮጲያ ለመጀመሪያ ጊዜ በጤና ተቋማት የሚከሰቱ ልደት እና ሞት ምዝገባን በሆስፒታል ውስጥ ማከናወን ተጀመረ

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና መረጃ ኤጀንሲ በተመረጠ የአዲስ አበባ ሆስፒታሎች ውስጥ ወቅታዊ የውልደት እና ሞት ምዝገባን ለማሻሻል ከጤና ቢሮ ጋር በመተባበር በዘውዲቱ ሆስፒታል በይፋ ማስጀመሩን በኤጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ ለብሰራት ሬዲዮ ተናግረዋል

ኢትዮጵያ ዝቅተኛ የልደት ምዝገባ ከሚያከናውኑ አምስት የአፍሪካ ሃገራት አንዷ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ዮናስ ወቅታዊ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ዝቅተኛ አፈፃፀም ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች ተለይተው ወደ ስራ ተገብቷል ብለዋል።

በአዲስ አበባ ለወቅታዊ የምዝገባ ዝቅተኛነት የተለያዩ ምክንያቶች የሚነሱ ሲሆን ወደ ወሳኝ ኩነት ምዝገባ እና መረጃ ጽ/ቤቶች መጥቶ ለማስመዝገብ ያለው ተነሳሽነት አናሳ መሆን እንዲሁም ወላጆች በአንድ ላይ ተገኝተው ለማስመዝገብ አለመቻላቸው ሰፊውን ድርሻ ይይዛል ።

ይህ አዲስ የምዝገባ አሰራር እናቶች ከጤና ተቋማቱ ወልደው ሳይወጡ የልደት ምዝገባ እንዲያከናውኑ የሚያስችል መሆኑን ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ በተመሳሳይምባ የሞት ምዝገባ በአፋጣኝ እንዲያገኙ መደረጉን አስረድተዋል፡፡

አሁን ላይ ከፍተኛ የውልደት መጠን በሚመዘገብባቸው አምስት ሆስፒታሎች የተጀመረ ሲሆን በቀጣይ ሁለት የፌደራል ሆስፒታሎችን ለማካተት በሂደት ላይ ይገኛል።

በሌላ በኩል የዲጂታል መታወቂያ ማተም ተግባር ክፍለከተማዎች የየራሳቸውን መታወቂያ ማተም እንዲችሉ የማሽን ግዢ እየተከናወነ ሲሆን ጊዜያዊ አዋጁ ሲነሳ ሁሉም የማተም ተግባር እንደሚጀምሩ አቶ ዮናስ ጨምረው ለብሰራት ሬዲዮ ተናግረዋል።

ቤተልሄም እሸቱ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *