በቡርኪናፋሶ ዋና ከተማ በሚገኘው የፕሬዚዳንቱ ቤተ መንግስት አካባቢ ወታደሮች በወሰዱት እርምጃ የተኩስ ድምፅ ይሰማ እንደነበር ከስፍራዉ የሚወጡ መረጃዎች አመላክተዋል። በትላንትናዉ እለት በኦጋዱጉ በሚገኙ በርካታ የጦር ሰፈሮች የተኩስ ድምፅ የተሰማ ሲሆን፣ ወታደሮች ወታደራዊ አለቆቻቻዉ ከስልጣን እንዲባረሩ እና ታጣቂ ቡድኖችን ለመዋጋት ተጨማሪ ግብአት እንዲሰጣቸዉ ጠይቀዋል።
በመቶዎች የሚቆጠሩ የከተማዋ ነዋሪዎች ወታደሮቹን ለመደገፍ አደባባይ የወጡ ሲሆን የቡርኪናፋሶ የመንግስት ባለሥልጣናት ዉጥረቱን ለመቆጣጠር የምሽት ሰዓት እላፊ አዋጅ እንዲያወጡ አስገድዷል፡፡መንግስት ቀውሱ በቁጥጥር ስር መዋሉን ተናግሯል።መፈንቅለ መንግስት ፈፅመዋል በሚል 11 ወታደሮች ከሳምንት በፊት በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኃላ አዲስ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ ነው መባሉን መንግስት ዉድቅ አድርጎታል፡፡
እ.ኤ.አ. ከ2015 ጀምሮ የምዕራብ አፍሪካን ግዛት ያወደመውን አማፂ ቡድን ማስቆም ባለመቻሉ በፕሬዚዳንት ሮክ ካቦሬ መንግስት ቅሬታ እየጨመረ ይገኛል፡፡
በሚኪያስ ፀጋዬ