
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በቭላድሚር ፑቲን ላይ የግል ማዕቀብ ሊጥሉ እንደሚችሉ አስታዉቀዋል።ሩሲያ በደቡብ-ምእራብ ድንበሯ ዩክሬን አቅራቢያ ባሰፈረችዉ ሀይል እርምጃ ብትወስድ ለዓለም “ትልቅ መዘዝ” ይኖረዋል ሲሉ ባይደን ተናግረዋል ።
ባይደን ይህንን አስተያየት የሰጡት ሌሎች የምዕራባውያን ሀገራት መሪዎች ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች ብዙ ዋጋ እንደምትከፍል ማስጠንቀቂያ ከሰጡ በኃላ ነዉ፡፡ሩሲያ በበኩሏ ውጥረቱን አሜሪካን እና ሌሎች ምዕራባዉያን ሀገራት እያባባሱት ይገኛል ወደ ዩክሬን የመግባት እቅድ እንደሌላት አስተባብላለች።
ሞስኮ ይህንን ትበል እንጂ በድንበር ወደ 100,000 የሚጠጉ የሩስያ ወታደሮች ተሰማርተዋል፡፡ከጋዜጠኞች ለተነሱ ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት ባይደን ሞስኮ ወረራ ከፈጸመች በፑቲን ላይ ማዕቀብ ይጣላል ሲሉ መልሰዋል፡፡
በዩክሬን ድንበር ላይ እንዲህ አይነት እርምጃ መውሰድ በአለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ መዘዝ እንደሚያስከትልና “ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ ትልቁን ወረራ” ሊያስከትል እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ባይደን አክለውም ኔቶ በምስራቅ አውሮፓ ያለዉን ሀይል የመጨመር ግዴታ እንዳለበት ይሰማኛል ብለዋል።
በስምኦን ደረጄ