መደበኛ ያልሆነ

ጥር 18፤2014-የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ቀሪ የሚሆንበትን ጊዜ በሚመለከት የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ውሳኔ እንዲሰጥበት የሚኒስትሮች ም/ቤት ወሰነ

የሚኒስትሮች ም/ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 2ኛ አስቸኳይ ስብሰባ የአገር ህልውና እና ሉዐላዊነት ላይ የተደቀነን አደጋ ለመከላከል የወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 5/2014 ቀሪ የሚሆንበትን ጊዜ በሚመለከት በቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

ሕወሃት እና ግብረአበሮቹ በአገራችን ህልውና እና ሉአላዊነት ላይ ከፍተኛ አደጋ የደቀኑ በመሆኑ እና ይህን አደጋ በመደበኛው የህግ ማስከበር ሥራ መከላከል የማይቻል ሆኖ በመገኘቱ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥቅምት 23 ቀን 2014 የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቁጥር 5/2014ን ያወጀ ሲሆን፣ ይህ አዋጅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርቦ በአዋጅ ቁጥር 1264/2014 ፀድቆ በሥራ ላይ የሚገኝ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ሆኖም ግን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማውጣት የግድ አስፈላጊ እንዲሆን አድርጎ የነበረው ሁኔታ የተቀየረ በመሆኑ እና ስጋቱን በመደበኛው የሕግ ማስከበር ስራ መከላከልና መቆጣጠር የሚቻልበት ደረጃ ላይ በመደረሱ ለስድስት ወራት የታወጀውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተፈፃሚነት ጊዜ ማሳጠር አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።

በመሆኑም በአዋጅ ቁጥር 1264/2014 አንቀጽ 11(2) በተደነገገው መሰረት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የስድስት ወራት የጊዜ ገደቡ ከመጠናቀቁ በፊት ለአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ መታወጅ ምክንያት የሆኑ ሁኔታዎች ከተቀየሩ እና በመደበኛው የሕግ ማስከበር ሥርዓት ሊከሰቱ የሚችሉ ጉዳዮችን መቆጣጠር ይቻላል ብሎ ካመነ የስድስት ወር ጊዜው ሳይጠናቀቅ ጊዜውን የማሳጠር ስልጣን ያለው በመሆኑ የአዋጁን ተፈጻሚነት ቀሪ እንዲያደርገው የሚጠይቅ የውሳኔ ሃሳብ ቀርቦ በውሳኔ ሃሳቡ ላይ የሚኒስትሮች ምክር ቤት በጥልቀት ተወያይቶ በማጽደቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ መወሰኑን ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *