መደበኛ ያልሆነ

ጥር 19፤2014-በአፋር ክልል አብአላ በኩል ወደ ትግራይ የሚደርስ እርዳታ ህወሓት በከፈተው ጦርነት እንደተስተጓጎለ መንግስት አስታወቀ

በአፋር ክልል አብአላ በኩል ወደ ትግራይ የሚላክ የሰብአዊ እርዳታ ህወሓት ዳግም በከፈተዉ ጦርነት መስተጓጎሉን የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ በሰጡት መግለጫ አስታዉቀዋል ። እንደ ሚስኒትሩ ማብራሪያ የእርዳታ እህል እና መድሀኒት የጫኑ ተሽከርካሪዎች ጉዟቸዉን ከጀመሩ በኋላ አሸባሪዉ በከፈተዉ ጦርነት ወደኋላ መመለሳቸውንም ተናግረዋል ። ቡድኑ ረሀብን ለፖለቲካ መጠቀሚያ እያደረገዉ ነዉ በማለትም ከሰዋል።

በተጨማሪም በወራሪዉ የህወሓት ቡድን በቁጥጥር ስር በቆዩ የአፋር እና የአማራ ክልሎች በተሟላ ሰላም ሁሉም የአስተዳደር እርከኖች ላይ ስራዎች እየተሰሩ ነዉ ሲል መንግስት አስታዉቋል።

በክልሎቹ የልማት እና የኢኮኖሚ ስራዎች እየተነቃቁ መሆኑንም ተናግረዋል ። በክልሎቹ አሉ የሚባሉ የጸጥታ ስጋቶችን የክልሎቹ መንግስት ከመፍታት በተጨማሪም የልማት ስራዎችን እያከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል ።

በጦርነቱ ሳቢያ ከተፈናቀሉ እና ድጋፍ ከሚሹ 1.4 ሚሊዮን ዜጎች ዉስጥ 1.2 ሚሊዮን የሚሆኑት ወደ ቀዬአቸው እንደተመለሱም ሚኒስቴሩ አስታውቀዋል። ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚደረገው ድጋፍም ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትም አስገንዝበዋል ።

በሶማሌ እና በኦሮሚያ ክልሎች እንዲሁም በደቡብ ኦሞ አካባቢዎች የተከሰተውን ድርቅ ለመቋቋም የፌደራል እና የክልል መንግስታት ጋር ችግሮችን ለመቃለል እየሰራ መሆኑንም በመግለጫቸው ተነስቷል።

በተጨማሪም በወይብላ ማሪያም በምዕመናን እና በጸጥታ አካላት መሀል የነበረዉን አለመግባባትም ለማጣራት መንግስት ከፌደራል ፖሊስ ፣ ከአዲስ አበባ ከተማ መስተዳድር እና ከኦሮሚያ ክልል የተወጣጣ የፖሊስ ግብረሀይል በማቋቋም ጉዳዩን እያጣራ እንደሚገኝ እና ዉጤቱም እንደተጠናቀቀ መንግስት የሚገልጽ መሆኑን ሚኒስቴሩ በመግለጫቸዉ አንስተዋል። ችግሩን ከመሰረቱ ለመቅረፍ የሀይማኖት አባቶች ፣ የሀገር ሽማግሌዎች ፣ ወጣቶች እና የአካባቢው አስተዳደሮች መሀል ዉይይት ለማድረግ እቅድ መያዙንም ሚኒስትሩ አክለዉ በመግለጫቸዉ አብራተዋል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *