
እሳት ሆነ ሌሎች ድንገተኛ አደጋ ሲያጋጥም ምላሽ ለማግኘት በሚደውልበት በ939 ነጻ የስልክ መስመር በቀን ከሚደወሉት ጥሪዎች 98 በመቶ ያህሉ ሀሰተኛ መሆናቸውን የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽኑ አስታውቋል፡የኮሚሽኑ የመረጃ ማዕከል ባለሙያ አቶ በየነ ጃለታ ለብስራት ሬድዮ እንደተናገሩት የአደጋ ጊዜ አስቸኳይ ጥሪ እንደሆነ እያወቁ ለቀልድ፣ ለፌዝ የሚጠቀሙት ሰዎች እጅግ በርካታ ሲሆኑ ይህም ስራቸውን አስቸጋሪ እንዳደረገው አንስተዋል፡፡
ወደ እሳትና ድንገተኛ የስልክ ጥሪ ደውለው ከሚጠየቁት ጥያቄዎች መካከል እንተዋወቅ፣ እጣ ፈንታዬን ንገሩኝ ፤ሞባይል ካርድ ሙሉልኝ ፤ትዳር ፈላጊ ነኝ እና መሰል ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪዎች የነፍስ አድን ጥያቄ ብቻ በሚስተናገድበት መስመር ይቀርባል። የኮሚሽኑ የመረጃና ስምሪት ክፍል ባለሙያዎች ለብስራት ሬድዮ እንደተናገሩት ከሆበ በእንዲህ ዓይነቱ ጥያቄ መስመሩ ሲጨናነቅ ከህብረተሰቡ ዘንድ ስልካችሁ አይሰራም ፣ተይዟል የሚሉ ቅሬታዎች ተደጋግመው ይሰማሉ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ፈጥኖ ለመድረስ እንቅፋት መሆኑን ተነግረዋል፡፡
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር አቶ አሸናፊ ቶላ ለጣቢያችን እንደተናገሩት ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል ቴክኖሎጂ ከመጠቀም ባለፈ ነጻ ጥሪ ከሚደረግበት ቁጥር በላይ ባለ መስመር ስልኮችን በኮሚሽኑ ዘጠኝ ቅርንጫፎች ለማስጀመር መታቀዱን ገልፀዋል።
በትግስት ላቀው