
የሰሜን ኮሪያ የመንግስት የመገናኛ ብዙሃን እንደዘገበዉ እ.ኤ.አ ከ2017 በኃላ በትናንትናዉ እለት ካካሄደው ትልቁ የሚሳኤል ሙከራን ተከትሎ ከህዋ ተነሱ የተባሉ ምስሎችን ይፋ አድርጓል። ምስሎቹ የኮሪያን ልሳነ ምድር እና ቀጠናዉን ከጠፈር ላይ የሚያሳዩ ናቸው፡፡
ሰሜን ኮሪያ ያስወነጨፈችዉ የባልስቲክ ሚሳኤሉ መካከለኛ ርቀት የሚምዘገዘግ ሀዉሶን 12 ተብሎ ይጠራል፡፡ ደቡብ ኮሪያ እና ጃፓን ሙከራውን ተከትሎ በሰጡት መግለጫ ሚሳኤሉ ጃፓን ባህር ላይ ከማረፉ በፊት 2,000 ኪሎ ሜትር ከፍታ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።
በተያዘዉ ወር ብቻ 7 ጊዜ የጦር መሳሪያ ሙከራን ሰሜን ኮርያ አድርጋለች፡፡
የጃፓን እና የደቡብ ኮሪያ ባለስልጣናት ሚሳኤሉ ለ30 ደቂቃ ያህል ወደ 800 ኪሎ ሜትር ርቀት መጓዙን ተናግረዋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሰሜን ኮሪያን የባልስቲክ እና የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ሙከራዎችን እንዳታደርግ ጥብቅ ማዕቀቦችን መጣሉ ይታወሳል፡፡
አንድ የዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ባለስልጣን ሰሜን ኮሪያ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ስለ ኒውክሌር እና ሚሳኤል መርሃ ግብሯ ቀጥተኛ ንግግር ማድረግ መጀመር አለባት ሲሉ ጥሪ ማቅረባቸውን ሮይተርስ ዘግቧል። ባለሥልጣኑ “አንዳንድ ከባድ ውይይቶችን ማድረግ መጀመር ሙሉ በሙሉ ተገቢ እና ፍጹም ትክክል ነው ብለን እናምናለን” ብለዋል፡፡
በስምኦን ደረጄ