መደበኛ ያልሆነ

ጥር 24፣2014-ለሁሉም የቅድመ ምረቃ ፕሮግራሞች የመውጫ ፈተና እንደሚሰጥ ተገለፀ !

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ከመንግስት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፕሬዚዳንቶች ጋር ተወያይተዋል፡፡

ውይይቱም በተቋማት ተጠያቂነትና የመረጃ ፍሰትን ለመዘርጋት እንዲሁም ውጤታማ እና ቀልጣፋ ሥራ እንዲያከናወኑ ያስችላል በተባለ የመንግስት ዩኒቨርሲቲዎች ረቂቅ መዋቅር ላይ ያተኮረ ነው።

በመንግስትም ሆነ በግል የከፍተኛ ትምህርት ጥራትን ወደሚፈለገው ደረጃ ከፍ ለማድረግ በቀጣይ የትምህርት ዘመን የመውጫ ፈተና ለሁሉም የቅድመ ምረቃ ፕሮግራሞች ሊሰጥ መሆኑን ሚኒስትሩ ጠቁመዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች የትምህርቱ ማህበረሰብ ከፖለቲካ ነፃ ሆነው ሃሳባቸውን የሚያንሸራሸሩባቸው ተቋማት መሆን እንዳለባቸውም አሳስበዋል፡፡

ፕሮፌሰር ብርሃኑ አክለውም ዩኒቨርሲቲዎች የእውቀት፣ የምርምርና የአዳዲስ ሃሳቦች መፍለቂያ ከመሆናቸው አንፃር ተልዕኳቸውን በብቃትና በውጤታማነት ለመፈፀም ይችሉ ዘንድ የተጀመረው የመዋቅር ሪፎርም ሥራ አንዱና ወሳኝ አካል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲዎች የአካባቢውን ማህበረሰብ ሕይወት ሊቀይሩ በሚቻሉበት መልኩ ከተልዕኳቸው ጋር አጠናክረው የሚሄዱበትን ጉዳይ ለይተው መሥራት እንደሚገባቸውም ገልፀዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ በተዘጋጀው የዩኒቨርሲቲዎች ረቂቅ መዋቅር ሰነድ ቀርቦ በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *