
በአዲስ አበባ በአትክልትና ፍራፍሬ ላይ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እየታየ ስለመሆኑ ቅሬታቸዉን ለብስራት ሬዲዮ ያቀረቡ ሸማቾች ገልጸዋል፡፡ሽንኩርት በኪሎ 25 ብር ቲማቲምን 34 ብር እየተሸጠ መሆኑን የተናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ በተለይ ቲማቲም በአንድ ሳምንት ውስጥ የ14 ብር ጭማሪ ማሳየቱን ሲያስረዱ እንዲሁም የተለያየ የአትክልት ምርቶች ላይ በሳምንት ውስጥ ያልተገባ ጭማሪ መታየቱ እንዳስደነገጣቸው አስረድተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በበኩሉ የዋጋ ንረት እንዳይከሰት የሚያስችሉ ስራዎች መሰራቱን በማስረዳት ሆኖም ግን ቢሮው በአሁኑ ወቅት ይሄ ነው የሚለው የዋጋ ንረት እንዲከሰት ያደረገ ጭማሪ አለመኖሩን የቢሮው የኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ዳንኤል ሚኤሶ በተለይ ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡
መንግስት ይህን የዋጋ ንረት እንዳይከሰት ለማድረግ በማሰብ ከወራት በፊት የእሁድ ገበያ ያስጀመረ መሆኑን ጠቅስው በነዚህ ገበያዎች ሱቆች ላይ ብሎም ወፍጮ ቤቶች ላይ ከሚሸጠው እጅጉን በቀነሰ መልኩ መቅረቡን አንስተዋል፡፡ህብረተሰቡ በነዚህ ገበያዎች መጥቶ እንዲገበያይ እድል በመፍጠር ገበያውን የማረጋጋት ስራ መሰራቱን ያነሱት አቶ ዳንኤል ቢሮው ባደረገው ግምገማ ምንም አይነት የዋጋ ንረት አለመኖሩን ጨምረው ተናግረዋል፡፡
ቤተልሄም እሸቱ