መደበኛ ያልሆነ

የካቲት 10፤2014-በፔኒስዮን ውስጥ ተኝተው የነበሩ ጥንዶች በእሳት አደጋ ህይወታቸው አለፈ

በአቃቂ ክ/ከተማ ወረዳ 6 በተለምዶ ሳሪስ ዘምባባ ጠጅ ቤት አካባቢ በንግድ ቤቶች እና የእንግዳ ማረፊያ ላይ በደረሰ ድንገተኛ የእሳት አደጋ በአንድ የመኝታ ክፍል ውስጥ ተኝተው የነበሩ ሁለት ሰዎችን ህይወት ሲያልፍ ሌሎች በእንግዳ ማረፊያ የነበሩ ሶስት ሰዎችን ከአደጋው ማትረፍ መቻሉን የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ኮሚሽን አስታውቋል።የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያው አቶ ንጋቱ ማሞ ለብስራት ሬድዮ እንደተናገሩት በአደጋው ህይወታቸው ያለፈውን የሁለቱን ግለሰቦች ማንነት እንዲሁም የአደጋውን መነሻ ምክንያት እስካሁን አለመታወቁን እና ፖሊስ እያጣራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ከፔንሲዮኑ ተያይዘው በሚገኙት አራት የንግድ ሱቆች፣ የእሳት አደጋው ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።ሰባት መቶ ሺ ብር የሚገመት ንብረትም በአደጋው የወደመ ሲሆብ ሰላሳ በሚሆኑ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ ባለሙያዎች በማሰማራት በአንድ ሰዓት ጊዜ ውስጥ እሳቱን ለመቆጣጠር ተችሏል።

በሌላ በኩል በኮልፌ ቀራንዮ ል/ከ ወረዳ 5 ልዩ ቦታው አየር ጤና አካባቢ በትላንትናው እለት በመኖሪያ ቤት ላይ በተነሳ የእሳት አደጋ ከአንድ መቶ ሺ በላይ የሚገመት ንብረት ሲወድም ከ ሁለት መቶ ሺ በላይ ንብረት ደግሞ ማትረፍ ተችሏል።

በትግስት ላቀው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *