መደበኛ ያልሆነ

ጥር 15፤2015-በአሜሪካ በቻይና አዲስ አመት ድግስ ላይ አንድ ታጣቂ በከፈተው ጥቃት 10 ሰዎች ተገደሉ

በዩናይትድ ስቴትስ የቻይና የጨረቃ አዲስ አመት በዓል ላይ ቅዳሜ እለት 10 ሰዎችን በጥይት የገደለው ታጣቂ ሲሸሽበት በነበረ መኪና ውስጥ ሞቶ መገኘቱን ፖሊስ አስታውቋል። በካሊፎርኒያ ግዛት የሚገኙ የፖሊስ መኮንኖች ግድያው በተፈፀመበት ከሞንቴሬይ ፓርክ በስተደቡብ ምዕራብ በምትገኘው ቶራንስ ከተማ ተሽከርካሪውን ከከበቡት በኋላ ግለሰቡ ራሱን አጥፍቶ አግኝተውታል።

ተጠርጣሪውን የ72 ዓመቱ ሁ ካን ትራን የሚባል ሲሆን ወደነበረበት ቫን ተሽከርካሪ ፖሊሶች ሲጠጉ ራሱ ላይ ተኩሷል።ሌሎች ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ያልዋሉ ሲሆን የጥቃቱ ምክንያቱ ግልፅ አለመሆኑ እና ሌሎች 10 ሰዎች መቁሰላቸውን ፖሊስ አስታውቋል።

ታጣቂው ሚስቱን እየፈለገ ነበር ሲሉ አንድ የአይን እማኝ የተናገሩ ሲሆን የተኩስ እሩምታ ያደረሰበትን ምክንያት ባናውቅም ታጣቂው ሚስቱን ለማግኘት ወደ ሞንቴሬይ ፓርክ የዳንስ ስቱዲዮ መጥቷል።የአይን እማኙ የታጣቂውን ግለሰብ ፎቶ በፖሊስ የተሰራጨው ሰው መሆኑን ማረጋገጥ ባይችሉም ልብሱ ግን ተመሳሳይ ይመስላል ብሏል።

ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የሞንቴሬይ ፓርክን ተኩስ ለመመርመር ሙሉ የፌደራል ድጋፍ ይደረጋል ሲሉ ተናግረዋል። በመግለጫቸው የጨረቃን አዲስ ዓመት ሲያከብሩ በነበሩ የእስያ-አሜሪካዊ እና የሃዋይ ተወላጅ፣ የፓሲፊክ ደሴት ነዋሪዎች ማህበረሰብ በጥይት መመታታቸውን አውግዘዋል። የሞንቴሬይ ፓርክ ወደ 60,000 የሚጠጋ ህዝብ የሚኖርበት ሲሆን ከነዋሪዎቹ 65 በመቶ የሚሆኑት እስያውያን ናቸው።

በስምኦን ደረጄ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *