መደበኛ ያልሆነ

ጥር 15፤2015-በጽኑ ህሙማን እና በሰመመን ዉስጥ ለሚገኙ ታካሚዎች አተነፋፈስ የሚረዱ ዘመናዊ የመተንፈሻ መሳሪያዎች ወደ ሀገር ዉስጥ ገቡ

ግራዲያን ኸልዝ ሲስተምስ የተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅት በጽኑ ህሙማን እና በሰመመን ዉስጥ ለሚገኙ ታካሚዎች አተነፋሰፈስ የሚረዱ ዘመናዊ የህክምና ማሽነሪዎችን ከአሜሪካ ሀገር አስገብቷል።

የግራዲያን ኸልዝ ሲስተምስ ተወካይ የሆኑት ዶ/ር ረድኤት ሽመልስ ለብስራት ራዲዮ እንደተናገሩት ፤ የበጎ አድራጎት ተቋሙ በቀጣይ ማሽኖቹን በሀገርዉስጥ ለማምረት እቅድ አንዳለዉ ገልፀው ፤ ለዚህም የጤና ሚኒስቴር ድጋፍ እያደረገላቸዉ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

ማሽኖቹ በሰመመን እና በጽኑ ህክምና ላይ ለሚገኙ ታካሚዎች አተነፋፈስ ምቹ ከመሆኑ በተጨማሪ በአንድ ግዜ እስከ 20 ለሚደርሱ ታካሚዎች አየር እንዲያገኙ የሚያስችል ማሽን እንዳስገቡም ተወካይዋ ጠቁመዋል።

በተጨማሪም ማሽኖቹ በኢትዮጵያ የጤና ዘርፍ እክል ለሆነዉ የሀይል መቆራረጥ መፍትሄ እንደሚሆኑ ዶ/ር ረድኤት አንስተዉ ፤ ከደቂቃዎች እና ሰዓታት ደምሮ እስከ ወራት ድረስ ማሽኖቹ ያለምንም የኤሌክትሪክ ሀይል በተገጠመላቸዉ ዘመናዊ ባትሪ አገልግሎት የሚሰጡ መሆናቸዉንም ተናግረዋል። አክለዉም ማሽኖቹን የበጎ አድራጎት ተቋሙ በተመጣጣኝ ዋጋ በመንግስትም ሆነ በግል ለሚገኙ የጤና ተቋማት ለማድረስ እቅድ መኖሩን ጠቅሰዋል፡፡

በኢትዮጵያ በተለይም በኮቪድ – 19 ወቅት በተለያዩ የጤና ተቋማት የኦክስጅን እጥረት አጋጥሞ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን አሁን ወደ ሀገር የገቡት ማሽኖች ይህን መሰል ችግር ለመቋቋም ትልቅ ሚና የሚኖራቸዉ መሆኑን የግራዲያን ኸልዝ ሲስተምስ ተወካይ የሆኑት ዶ/ር ረድኤት ሽመልስ ጨምረው ለብስራት ራዲዮ ተናግረዋል።

በበረከት ሞገስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *