መደበኛ ያልሆነ

ጥር 15፤2015-የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 88 በመቶ ደረሰ

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በመላዉ ኢትዮጲያ የሚደረገዉ ድጋፍ ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን የግድቡ ግንባታ በአሁኑ ወቅት 88 በመቶ መድረሱን የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት አስታውቋል።የጽሕፈት ቤቱ የሚዲያና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ኃይሉ አብርሃም ለብስራት ሬዲዮ እንደተናገሩት በሃገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ግድቡ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ እስከ ኀዳር 30 ቀን ድረስ ከ17 ቢሊዮን 595 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ድጋፍ መሰብሰቡን ገልጸዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ ባለፉት አራት ወራት ብቻ 702 ሚሊየን 709 ሺህ ብር ገቢ መሰብሰቡን የሚታወስ ሲሆን በሀገር ውስጥና በዳያስፖራ ቦንድ ግዥና ስጦታ፣ በ8100 አጭር የጽሑፍ መልዕክት እንዲሁም በሌሎች የድጋፍ ማሰባሰቢያ መንገዶች ገቢው መሰብሰቡን አብራርተዋል።በተጨማሪም የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የተቀመጠበትን 12ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ የተለያዩ ሁነቶችን በማዘጋጀት ገቢ ለመሰብሰብ ዕቅድ መያዙንም ጠቁመዋል፡

የሕዳሴ ግድብ አስተባባሪ ፅ/ቤት ከጥር 17 እስከ ጥር 26 ቀን 2015 ድረስ በአዲስ አበባ በአባይ ወንዝ መነሻ ላይ ያተኮረ ከ23 ሀገራት የተውጣጡ ሰዓሊያን የሚሳተፉበት መነሻ ወይም Origin ኢንተርናሽናል የስዕል ሲምፖዚየም እና ወርክሾፕ መዘጋጀቱን አቶ ሀይሉ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል፡፡ይህ የአለማችን ታላላቅ ሰዓሊያን የሚሳተፉበት ሁነት ለኢትዮጲያ በጎ ገጽታ ግንባታ መጎልበት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ቤተልሄም እሸቱ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *