መደበኛ ያልሆነ

ጥር 16፤2015-በትላንትናው እለት በተከሰቱ ሶስት የእሳት አደጋዎች በ10 ሰዎች ላይ ጉዳት ሲደርስ ከ2.5 ሚሊየን ብር በላይ የተገመተ ንብረት ወድሟል

👉 የለሚ ኩራ ክፍለ ከተማ ለተጨማሪ አገልግሎት የተከራየው ህንጻ ውድመት ደርሶበታል

በአዲስ አበባ እና ዙሪያዋ ትላንት ጥር 15 ቀን ሶስት የእሳት አደጋዎች የተከሰቱ ሲሆን ከ2.5 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ሲወድም 10 ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን የእሳት አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለብስራት ሬዲዮ እንደተናገሩት ትላንት ከቀኑ 10:46 በሸገር ከተማ ቡራዩ በሹፋን ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ ከ300 ሺህ ብር በላይ የተገመተ ንብረት ወድሟል።

በሌላ በኩል ምሽት 3:55 በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 5 አስኮ መነሀሪያ በህዝብ ማመላለሻ አዉቶቢስ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ 1 ሚሊየን ብር የተገመተ ንብረት ወድሟል።

እንደዚሁም ምሽት 4:58 ባለ 7 ወለል ህንጻ ላይ በደረሰ የእሳት አደጋ ከ1.6 ሚሊየን ብር በላይ የተገመተ ንብረት ሲወድም በ10 ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን አቶ ንጋቱ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል። ከተጎጂዎቹ መካከል ሶስቱ የእሳት አደጋ ሰራተኞች ናቸዉ።

የእሳት አደጋዉ ከህንጻዉ ምድር ቤት የተነሳ ሲሆን እሳቱ እስከ ሁለተኛ ፎቅ ድረስ ጉዳት አድርሷል። ህንጻዉ ለለሚ ኩራ ክፍለ አስተዳደር ለተጨማሪ የቢሮ አገልግሎት የተከራየ ሲሆን ስራ ለመጀመር በሂደት ላይ የነበረ መሆኑም ታውቋል።

ሶስቱንም የእሳት አደጋዎች ለመቆጣጠር 8 የአደጋ መቆጣጠር ተሽከርካሪና 2 አምቡፑላንስ ከ65 የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ጋር የተሰማራ ሲሆን አደጋዎቹን ለመቆጣጠር በተደረገ ጥረት ከ250 ሚሊየን ብር በላይ የተገመተ ንብረት ማዳን ተችሏል።

በትግስት ላቀው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *