
በዩናይትድ ስቴትስ በዋይት ሀውስ አቅራቢያ በሚገኝ የደህንነት ስፍራ ከተከሰተዉ የከባድ ተሸከርካሪ ግጭት በኃላ አንድ የ19 ዓመት ታዳጊ ወጣትና የናዚ አንድናቂ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ለመግደል ወይም ለመጉዳት በመዛቱ ክስ ተመስርቶበታል፡፡ተጠርጣሪዉ ሳይ ቫርሺት ካንዱላ የሚባል ሲሆን ሰኞ እለት የጭነት ተሸከርካሪዉን በማጋጨት የናዚን ባንዲራ ሲያውለብለብ እንደነበር ተነግሯል፡፡
በተሸከርካሪዉ አደጋ የተጎዳ ሰው የለም። በጭነት መኪናው ውስጥ ፈንጂም ሆነ የጦር መሳሪያ አልተገኘም።ካንዱላ ህንዳዊ እንደሆነ ተነግሯል፡፡ባይደን በደህንነት ስፍራዉ በሆነዉ በፓርክ ፖሊስ ስለደረሰው አደጋ ገለጻ ተደርጎላቸዋል ሲሉ የዋይት ሀውስ የፕሬስ ፀሐፊ ካሪን ዣን ፒየር ተናግረዋል ። ከስፍራዉ በወጡ ምስሎች በጭነት መኪናው ላይ ፖሊስ ባደረገው ፍተሻ የተገኘውን ቀይ እና ጥቁር የናዚ አርማ የሆነዉ የስዋስቲካ ባነር መመልከት ተችሏል፡፡
ክሪስ ዛቦጂ የተባለ የአይን እማኝ ሹፌሩ ቢያንስ ሁለት ጊዜ የደህንነት ስፍራዉን ሰብሮ እንደገባ ተናግረዋል።የድርጊቱ ፈጻሚ ካንዱላ ለወራት እቅድ ካወጣ በኋላ ትኬት በመቁረጥ ከሴንት ሉዊስ ወደ ዋሽንግተን መምጣቱን ለሚስጥራዊ አገልግሎት ወኪሎች ተናግሯል፡፡”ወደ ኋይት ሀውስ በመድረስ፣ ከባይደን ስልጣኑን ለመንጠቅ እና የሀገሪቱን ሀላፊ ለመሾም” ፈልጎ እንደነበር በክስ መዝገቡ ላይ ቀርቧል፡፡
በስምኦን ደረጄ