መደበኛ ያልሆነ

ግንቦት 17፤2015-ከመቃብር ሀውልት ግንባታ ጋር ተያይዞ እስከ 40ሺህ ብር ሲያስከፍል የነበረ የቀብር አስፈጻሚ ማህበር ከስራ ታገደ

በሀዉልት ግንባታ ከተሰማሩ 28 ማህበራት መካከል ለሀዉልት ግንባታ በሚል ከ30 እስከ 40 ሺህ ብር ድረስ ሲያስከፍሉ በነበሩ ሌሎች የቀብር አስፈጻሚ ማህበራት ላይም የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዱን  በአዲስ አበባ ከተማ አሰተዳደር የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ አስታወቀ፡፡በቢሮው ምክትል ቢሮ ሃላፊ የሆኑት ወ/ሮ ይመኙሻል ታደሰ ለብስራት ሬድዮ እንደተናገሩት በቢሮው የተተመነው ደረጃ አንድ የሚባለው የሃውልት ግንባታ ወጪ 8ሺህ 1መቶ 81 ብር ሲሆን ደረጃ ሶስት የሚባለው ደግሞ  3ሺህ 5 መቶ 2 ብር እንዲሆን ተወስኗል፡፡

ይሁን እንጂ ይህን ህግ በመጣስ ከ30 እስከ 40ሺህ ብር ድረስ የሚያስከፍሉ በርካታ የቀብር ስነ ስርአት አስፈጻሚ ማህበራት በአዲስ አበባ መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡በቢሮው የተቀናጀ ዘላቂ  ማረፊያ አስተዳደር የሆኑት አቶ አጃይብ ኩምሳ በበኩላቸው አላስፈላጊ ወጪን ለሃውልት ግንባታ ሲጠይቅ የነበረ አንድ ማህበር እንዲታገድ መደረጉን እንደዚሁም ለተቀሩት በርካታ የቀብር አገልግሎት ሰጪ ማህበራት የተለያዩ ማስጠንቀቂያዎች እንደተሰጣቸውም  ተናግረዋል፡፡

ችግሩን ለመፍታት ቢሮው በቅርቡ  የተቀመጡ ደረጃዎችን ጠብቀው ስራቸውን ማከናወን እንዲችሉ ከማህበራቱ ጋር የምክክር መድረክ ለማካሄድ አቅጃለሁ  ብሏል፡፡እንደዚሁም የፍቃድና የብቃት ማረጋገጫን ከቢሮው ወስደው በአግባቡ የቀብር አገልግሎትን መፈጸም እንዲችሉ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረጋል ተብሏል፡፡

በቅድስት ደጀኔ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *