መደበኛ ያልሆነ

ግንቦት 17፤2015-የዋግነር ቡድን በባክሙት ውጊያ 20 ሺ ወታደሮቹ እንደተገደሉበት አስታወቀ

???? ቦልሼቪክስ ወደ ስልጣን ሲወጣ የተከሰተውን የ1917ቱን ዓይነት ብጥብጥ ሩሲያ ያሰጋታል

በምስራቅ ዩክሬን የምትገኘውን የባክሙት ከተማን ለመቆጣጠር ለወራት ከዘለቀው ጦርነት በኃላ የሩሲያው ዋግነር ቅጥረኛ  ቡድን 20,000 የሚጠጉ ወታደሮቹ መገደላቸውን የቡድኑ መስራቹ ተናግረዋል፡፡የዋግነር መስራች የሆኑት የቭጀኒ ፕሪጎዝኒ በጦርነቱ ከዩክሬን ጋር ዋግነር ለመዋጋት ወደ 50,000 የሚጠጉ እስረኞችን እንደመለመለ እና ከእነዚህ ውስጥ 20ሺ ያህሉ መገደላቸዉን ይፋ አድርገዋል፡፡

መሪዉ በቴሌግራም ገፅ ላይ በተለቀቀ የቪዲዮ ቃለ ምልልስ ከሩሲያ የፖለቲካ ስትራቴጂስት ለኮንስታንቲን ዶልጎቭ ጋር ቆይታ አድርገዋል። የኮንትራት ወታደሮቹ በከተማይቱ ጦርነት ጠፍተዋል አልያም የደረሱበት አልታወቀም ሲሉም አክለዋል።

ዋግነር እና የሩሲያ ጦር በረዥም ጦርነት ባክሙትን መቆጣጠራቸዉን ባሳለፍነዉ ቅዳሜ ማሳወቃቸዉ የሚታወስ ሲሆን የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የታጠቁ ሀይሎችን እንኳን ደስ አላችሁ ማለታቸው አይዘነጋም። ነገር ግን ዩክሬን ባክሙት ከእጇ እንዳልወጣ አሁንም ትናገራለች።

ከአንድ አመት በፊት ሩሲያ ሙሉ በሙሉ በዩክሬን ላይ ወረራ ከጀመረች በኋላ በሩሲያ ፖለቲካ ውስጥ ተፅእኖቸው እየጠነከረ የመጣው የዋግነር መሪ ፕሪጎዝሂን የሩሲያ ወታደራዊ አመራርን ብሎም የመከላከያ ሚኒስትሩን ሰርጌይ ሾይጉ የሚተቹ ሲሆን የጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ቫለሪ ገራሲሞቭን በብቃት ማነስ ይከሳሉ።

የዋግነሩ አለቃ ይህ ዓይነቱ ሁኔታ ከቀጠለ በቭላድሚር ሌኒን ይመራ የነበረው ቦልሼቪክስ ወደ ስልጣን ሲወጣ የተከሰተውን የ1917ቱን ዓይነት ብጥብጥ ሩሲያ ሊያጋጥማት እንደሚችል አስጠንቅቀዋል።

በስምኦን ደረጄ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *