መደበኛ ያልሆነ

ሰኔ 9፤2015-በአዲስአበባ ከ 25 ሺህ በላይ በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶች እንዳሉ ይገመታል ተባለ

የአዲስአበባ ከተማ መስተዳድር ጤና ቢሮ በከተማዉ ከ 25 ሺህ በላይ በወሲብ ንግድ ላይ የተሰማሩ ሴቶች እንዳሉ ይገመታል ሲል አስታዉቋል።

በቢሮዉ የኤች አይ ቪ ኤድስ ተፅዕኖ ቅነሳና ሀብት ማሰባሰብ ቡድን መሪ አቶ የማነ ገብረመስቀል ይህ ቁጥር ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል ጠቁመዋል። አሁን ላይም ዘርፉ መልኩን እየቀየረ በጋራ መኖሪያቤቶች በስፋት እየታየ መሆኑን ገልጸዋል። ከነዚህም ዉስጥ የጎተራ እና የካ አባዶ የጋራ መኖሪያ መንደሮች ላይ በርካታ ሴቶች “ቅምጥ” በመሆን ከተለያዩ ወንዶች ጋር ግንኙነት እንደሚኖራቸዉ በጥናት ተረጋግጧል ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ በሆቴሎች ፣ ሬስቶራንቶች ፣ ማሳጅ ቤቶች እና በመንገድ ዳር በሚቆሙ ሴቶች እንደሚፈጸም ገልጸዋል።

ቢሮዉ በአዲስአበባ በአሁኑ ወቅት የኤች አይ ቪ ኤድስ ስርጭት 3.36 በመቶኛ ላይ መድረሱንም ገልጿል። የአዲስአበባ ጤና ቢሮ በየጊዜዉ በበሽታዉ እየተያዙ ያሉ ሰዎች ቁጥርን መቀነስ መቻሉን አቶ የማነ ገብረመስቀል መናገራቸዉን ብስራት ራዲዮ ሰምቷል። ሆኖም የቫይረሱ ስርጭት ከ 1 በመቶኛ በላይ ከሆነ በወረርሽኝ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ የአለም ጤና ድርጅት ይገልጻል።

እ.ኤ.አ 2021 አመት በተሰራ ጥናት በመላዉ አለም ከ 38 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ቫይረሱ በደማቸዉ እንዳለ ተረጋግጧል። ከነዚህም ዉስጥ 1.7 ሚሊዮን የሚሆኑት ህጻናት ሲሆኑ የቫይረሱ ስርጭት ከሰሃራ በታች ደግሞ ከፍተኛ መሆኑ ተመላክቷል።

በአዲስአበባ የወሲብ ንግድ በዚህ ደረጃ መስፋፋቱ ኢኮኖሚያዊ አስገዳጅ ሁኔታዎች ከፍተኛዉን ድርሻ እንደሚይዙ የተነሳ ሲሆን ተግባሩ በህግ የተከለከለ አለመሆኑም ለመበራከቱ ሌላኛው ምክኒያት መሆኑ ተነስቷል። የቫይረሱ ስርጭትም በዚህ ዘርፍ በተሰማሩ ሴቶች ላይ ከፍተኛ መሆኑ ተገልጿል።

በበረከት ሞገስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *