መደበኛ ያልሆነ

ሰኔ 12፤2015-በአሜሪካ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ አምስት ኢትዮጵያዊያን ሴቶች ለሰርግ ስነስርዓት ሲሰናዱ በመኪና አደጋ ህይወታቸው አለፈ

በሰሜን አሜሪካ ሚኒሶታ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ አምስት ኢትዮጵያዊያን ሴቶች ባሳለፍነዉ አርብ በመኪና አደጋ ህይወታቸዉ ማለፉ ተሰምቷል።

ኢትዮጵያዊያኑ ቅዳሜ ለሚካሄድዉ የሰርግ ስነስርዓት ቁሳቁሶችን ሸምተዉ ወደ መኖሪያቸው ሲመለሱ አደጋዉ ማጋጠሙ ተዘግቧል። ሁለት የ 20 እና ሁለት የ 19 አመት ወጣቶች እንዲሁም አንድ የ 17 አመት ታዳጊ ህይወታቸዉን በአደጋው ማጣታቸዉን ብስራት ራዲዮ በአሜሪካ ከሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ሰምቷል።

በመኪና አደጋዉ ከሌላ መስመር በከፍተኛ ፍጥነት ከመጣ ተሽከርካሪ ጋር በተከሰተ ግጭት ህይወታቸዉ አልፏል። አሽከርካሪዉ አደጋዉን ካደረሰ በኋላ ከመኪናዉ በመዉጣት ሮጦ ለማምለጥ ሞክሯል።

በአካባቢው በነበሩ ሰዎች ጥቆማ መሰረት ግለሰቡን የሚኒያፖሊስ የጸጥታ አካላት በቁጥጥር ስር አዉለዉታል ተብሏል። በተደረገለት ምርመራም ግለሰቡ አልኮልና አደንዛዥ እፅ ተጠቅሞ ሲያሽከረክር እንደነበረ ተረጋግጧል።

በሚኒሶታ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የሶማሌ ተወላጆች በከፍተኛ ሀዘን ዉስጥ መሆናቸዉንም ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል። ማህበረሰቡም
ለተጎጂ ቤተሰቦች እስካሁን 300 ሺህ የአሜሪካን ዶላር ማሰባሰቡም ተገልጿል።

በተመሳሳይ በአሜሪካ ኒዉዮርክ ከተማ አንድ ኢትዮጵያዊ የሜትር ታክሲ አሽከርካሪ ተሳፋሪ መስለዉ ጥቃት በሰነዘሩበት ሰዎች የአካል ጉዳት እንደደረሰበት ተሰምቷል። ግለሰቡን ከመኪናዉ ካወረዱ በኋላ ጥቃት አድራሾቹ ተሽከርካሪዉን ይዘዉ ተሰዉረዉ ነበር። ከፖሊስ በቂ እርዳታ አላገኘሁም ያለዉ ኢትዮጵያዊዉ በኋላም በአንድ ጋዜጠኛ እርዳታ ዳግም መኪናዉን ማግኘት እንዳልቻለ ተዘግቧል።

በበረከት ሞገስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *