መደበኛ ያልሆነ

ሰኔ 23፤2015-የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶችን አስቁመው በመዝረፍ ሲፈለጉ የነበሩ ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

በሸካ ዞን ቴፒ ከተማና አካባቢው በተለያዩ ጊዜያቶች የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶችን አስቁመው በመዝረፍ ሲፈለጉ የነበሩ ሁለት ግለሰቦች በጋምቤላ ክልል በቁጥጥር ስር ውለው ለደቡብ ምዕራን ኢትዮጵያ ክልል ተላልፈው እንደተሰጡ ተነግሯል ።

ግለሰቦቹ የህዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶችን አስቁመው በተደጋጋሚ በመዝረፍ የሽፍታነት ተግባር በመፈፀም ወንጀል በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወጥቶ ሲፈለጉ መቆየታቸው ተገልጿል ። ከአሁን ቀደም በዚሁ ተግባር ተሳትፎ የነበራቸው ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ውለው የተወሰኑት በህግ ሲጠየቁ የተወሰኑት በይቅርታ ታልፈዋል።

እነዚህ ሁለት ግለሰቦች ግን ጠፍተው ሲፈለጉ መቆየታቸውን በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነትና ኮሚኒኬሽን ዳይሬክቶሬት ምክትል ኢንስፔክተር ደጀኔ አሰፋ ለብስራት ራዲዮ ተናግረዋል።ወንጀል ፈፃሚዎች ገንዘብ ፣ ሞባይል ስልክ ፣ ጌጣጌጥ እና ሌሎች ንብረቶችን ሲዘርፉ እንደነበር የተገለፀ ሲሆን  በጋምቤላ ክልል በክልሉ ፖሊስ በቁጥጥር ስር ውለው ለሸካ ዞን ፖሊስ መምሪያ ተላልፈው ተሰጥተዋል ።

ግለሰቦቹ እንዲያዙ የጋምቤላ ክልል ፖሊስ እና ህብረተሰቡ ላደረገው ትብብር የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽኑ ምስጋና እንደሚያቀርብ ምክትል ኢንስፔክተር ደጀኔ አሰፋ ለብስራት ራዲዮ ተናግረዋል ።

በአበረ ስሜነህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *