መደበኛ ያልሆነ

ሰኔ 26፤2015-መንገዶችን በሚያበላሹ የጭነት ተሽከርካሪዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ሊጀመር ነው

የመንገድ መሰረተ ልማት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለማስቀረት እንዲሁም በትራፊክ ፍሰት እና ደህንነት ላይ ተፅእኖ የሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎች ለማስቀረት ከትራፊክ ፖሊስ ጋር በመቀናጀት ጥብቅ ቁጥጥር ሊጀምር መሆኑት በአዲስ አበባ ትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ብርሃኑ ኩማ በተለይ ለብሰራት ሬዲዮ ተናግረዋል።

በከተማዋ እየተገነቡ  ከሚገኙ የተለያዩ የግንባታ ቦታዎች ተረፈ ምርቶችን እና አፈር እየጫኑ የሚንቀሳቀሱ የጭነት ተሽከርካሪዎች መንገዶችን  ከማበላሸታቸው እና ከማቆሸሻቸው ባሻገር  ለእግረኞች እና ለተሽከርካሪዎች ከፍተኛ ስጋት እየሆኑ ስለሚገኙ ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል ተብሏል።

ተሽከርካሪዎቹ የጫኑትን ተረፈ ምርቶችና አፈር ሳይሸፍኑ ስለሚንቀሳቀሱ አስፓልቱን እያቆሸሹ የሚገኙ ሲሆን ተረፈ ምርቱን ጭነው ሲወጡ በጎማዎቻቸው ይዘው ወደ አስፈልት በሚወጡት ጭቃም መንገዱን በከፍተኛ ሁኔታ እያቆሸሹ ይገኛል።

ኤጀንሲው ከአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ጋር በመሆን መሰረተ ልማቱን የሚጎዳ፣ የአሽከርካሪዎች እና የእግረኞች እንቅስቃሴ ላይ የመንገድ ደህንነት ስጋት የሚፈጥር እንዲሁም የከተማዋን መንገዶች የሚያቆሽሹ አሽከርካሪዎች በልዩ ሁኔታ ጥብቅ ቁጥጥር ያደርጋል።

በትራፊክ ጭነት ላይ ተገቢውን ምልክት ሳያደርግ ወይም ተሽከርካሪው ላይ የተጫነውን ጭነት በሚገባ ሳያስር ወይም ሳይሸፍን ያሽከረከረ እንዲሁም በመንገድ ላይ ያፈሰሰውን ወይም የጣለውን ፈሳሽ ወይም ጠጣር ነገሮችን ያላነሳ ወይም ያላጸዳ አሽከርካሪ ቅጣት የሚጣልበት መሆኑን ተጠቁሟል።   የተለያዩ ግንባታዎችን እያከናወኑ የሚገኙ ተቋማት ባለቤቶች እና የጭነት ተሽከርካሪ አሽከርካሪዎች የሚጭኑ ተረፈ ምርቶች እና አፈር መንገድ ላይ እንዳይፈሱ በመሸፈን፣ ወደ አስፋልት ሲወጡ የተሽከርካሪያቸውን ጎማ በማጽዳት መንገድ ላይ መንቀሳቀስ እንዳለባቸው ተጠቀሟል።

ከተቀመጠው የእንቅስቃሴ ቅድመ ጥንቃቄዎች ውጭ በመንቀሳቀስ የከተማዋን አስፓልት ከማባላሸት እና ከማቆሸሽ ባሻገር ለእግረኞች እና ለተሽከርካሪዎች እንቅስቃሴ ስጋት የሚሆኑ ተሽከርካሪዎች ላይ የኤጀንሲው የትራፊክ ተቆጣጣሪዎች እና ትራፊክ ፖሊሶች በጋራ ጥብቅ ቁጥጥር በማድረግ ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ አቶ ብርሃኑ ኩማ ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ ተናግረዋል።

በኤደን ሽመልስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *