መደበኛ ያልሆነ

ሐምሌ 18፤2015-በአልጄሪያ በተቀሰቀሰው ሰደድ እሳት የ34 ሰዎች ህይወት አለፈ

በመላው አልጄሪያ በተቀሰቀሰው ሰደድ እሳት ቢያንስ 34 ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን የአልጄሪያ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል። በ16 አውራጃዎች 97 ሰደድ እሳት በደን፣ በሰብል እና በእርሻ መሬት ላይ በትላንትናው እለት ጉዳት አድርሷል።

ወደ 8,000 የሚጠጉ የእሳት አደጋ ተከላካዮች እሳቱን በቁጥጥር ስር ለማዋል እየሰሩ መሆናቸውን ባለስልጣናቱ ተናግረዋል። በተጨማሪም 26 ሰዎች የቆሰሉ ሲሆን 1,500 ያህል ሰዎች በፌናያ፣ ቤጃያ፣ ዝባርባር እና ቡዪራ ከመኖሪያ ቤታቸው ተፈናቅለዋል። በቤጃያ በተነሳው የእሳት ቃጠሎ 10 ወታደሮች መሞታቸውን የአልጄሪያ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል።

ከአልጀርስ በስተምስራቅ ተራራማ ካቢሊ ክልል ውስጥ እጅግ በጣም ሰፊ የሆነ ሰደድ  እሣት በከፍተኛ ንፋስ እየተገፋ በቤጃያ እና ጂጄል የባህር ዳርቻ ከተሞች ወደሚገኙ የመኖሪያ አካባቢዎች እየተሰራጨ ይገኛል።የቃጠሎው መንስዔ ላይ የፍትህ አካላት ምርመራ መጀመራዠውን የሀገሪቱ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።

በሰሜናዊ አልጄሪያ በቅርብ ቀናት ውስጥ ከፍተኛ ሙቀት እየተመዘገበ ሲሆን የሙቀት መጠኑ 48 ዲግሪ ሴንቲግሬድ  ደርሷል። በሰሜን አፍሪካ ውስጥ በተለያዩ ክልሎች ያለው የሙቀት መጠን ከመደበኛው እስከ 7 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ከፍ ብሏል።የአልጄሪያ የሚቲዎሮሎጂ ጽህፈት ቤት በሰሜናዊ የሀገሪቱ ክፍል ከ48 ዲግሪ ሴንቲግሬድ በላይ የሙቀት መጠኑ እስከ ወሩ መጨረሻ ሊቀጥል እንደሚችል አስጠንቅቋል።

በስምኦን ደረጄ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *