መደበኛ ያልሆነ

ሐምሌ 21፤2015-በአለፋ ወረዳ ከአስር ወራት በላይ የኤሌክትሪክ አገልግሎት በመቋረጡ አንድ ሞባይል ስልክ ቻርጀር ለማድረግ ነዋሪዎች እስከ 30 ብር ድረስ ይከፍላሉ

በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በአለፋ ወረዳ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከተቋረጠ ከአስር ወር በላይ መሆኑንና የኤሌክትሪክ አገልግሎቱ በመቋረጡ ለከፋ ችግር መዳረጋቸውን ነዋሪዎች ለብስራት ራዲዮ ተናግረዋል ።ነዋሪዎች እንደሚሉት ችግሩ እንዲፈታ በ2015 በጀት ዓመት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ጥያቄ ተነስቶ ነበር ብለዋል ።

ይኸውን ጉዳይ ለመፍታት የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ምላሽ እንደሚሰጥ  ቃል የተገባ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ተግባራዊ እንዳልሆነ አክለዋል ። ውሃን በተመለከተ በአሁኑ ወቅት የከተማ አስተዳደሩ የውሃ ቦቲ በማዘጋጀት በየቀበሌው እየተዘዋወረ በጀሪካን 10 ብር እያቀረበ ቢገኝም በቂ ባለመሆኑ እንደ አማራጭ የዝናብ ውሃ እየተጠቀሙ መሆናቸው ነዋሪዎች  ተናግረዋል ።

የችግሩ አሳሳቢነት በኤሌክትሪክ እና በዉሃ ብቻ የሚያበቃ ሳይሆን በወረዳው የኤሌክትሪክ አገልግሎት ከተቋረጠ በኋላ የማኒፋክቸሪንግ ዘርፉን ጨምሮ ሌሎች የስራ ዘርፎችም እየተፈተኑ እንደሚገኝ ተናግረዋል ። ከነዚህም ውስጥ የወፍጮ ቤት አገልግሎት ለማግኘት  መብራት ባለመኖሩ በናፍጣ ለሚሰሩ ወፍጭ ቤቶች በከፍተኛ ዋጋ እያስፈጨን እንገኛለን ብለዋል ።

ሞባይል ስልክ ቻርጀር ለማድረግ ፈተና እንደሆነባቸው የተናገሩ ነዋሪዎች በጀነኔተር እስከ 30 ብር ድረስ ለአንድ ሞባይል ስልክ እንደሚከፍሉ ለብስራት ሬዲዮና ቲቪ ተናግረዋል ።ከአለፋ ወረዳ በቅርብ ርቀት የጣና በለስ ኃይድሮ ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ ማእከል እንደሚገኝ የተናገሩ ሲሆን የጣና በለስ ስኳር ፋብሪካን ጨምሮ ሌሎችም አካባቢዎች ከዚሁ የሀይል ማመንጫ ተጠቃሚ መሆናቸውን ተናግረዋል ።

ነገር ግን የአለፋ ወረዳ ነዋሪዎች በኤሌክትሪክ እጦት እየተሰቃየን እንገኛለ ሲሉም አክለዋል ። ከአሁን ቀደም የጣና በለስ የስኳር ፋብሪካ ከሚያገኘው ሀይል የሚተርፈውን ሀይል በመጠቀም የኤሌክትሪክ ችግሩ እንዲፈታ ይደረጋል ተብሎ የነበረ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ችግሩ ሳይፈታ ቀጥሏል ብለዋል ።

ጉዳዩን በተመለከተ ብስራት ራዲዮና ቲቪ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የጠየቀ ሲሆን የአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ምላሽ የማይሰጥ ከሆነ ብቻ በኛ በኩል መልስ ይሰጣል ብሏል ። በተባለው መሰረት ከአማራ ክልል ኤሌክትሪክ አገልግሎት ምላሽ ለማግኘት ብስራት ሬዲዮና ቲቪ በተደጋጋሚ ያደረገው ሙከራ ለጊዜው አልተሳካም ።

በአበረ ስሜነህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *