የኒጀር ጦር ከስልጣን የተባረሩትን ፕሬዝዳንት ሞሃመድ ባዙምን በሀገር ክህደት ክስ እንደሚመሰርት አስታዉቋል፡፡
ይህ የተሰማዉ የሀገሪቱ ከፍተኛ የምሁራን ቡድን የመፈንቅለ መንግስቱ መሪዎች ከምዕራብ አፍሪካ ቀጣናዊ ቡድን ጋር ያላቸውን አለመግባባት ለመፍታት ለዲፕሎማሲ ክፍት መሆናቸውን ካሳወቁ ከሰዓታት በኋላ መሆኑ ተነግሯል።በብሔራዊ ቴሌቪዥን ላይ በተነበበ መግለጫ የኒጀር ጦር ቃል አቀባይ በባዙም ላይ “ከፍተኛ የአገር ክህደት እና የሀገሪቱን የውስጥ እና የውጭ ደህንነትን የሚጎዳ ተግባር በመፈጸም” የሚል ክስ አቅርበዋል ።
የ63 አመቱ ባዙም እና ቤተሰባቸዉ በኒያሚ በሚገኘዉ የፕሬዝዳንቱ ቤተ መንግስት ዉስጥ በእስር ላይ ይገኛሉ ።የምዕራብ አፍሪካ ኢኮኖሚ ማህበረሰብ ባዙም ወደ ስልጣናቸዉ እንዲመለሱ ጠይቋል፡፡ ይህ ካልሆነ በኒጀር ላይ ከባድ የኢኮኖሚ ማዕቀብ በመጣል እና የሲቪል አገዛዝ ካልተመለሰ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት እንደሚኖር ዝቷል፡፡
በኒጀር “ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ወደነበረበት ለመመለስ ተጠባባቂ ኃይል” እንዲሰማራ ያፀደቀው የምዕራብ አፍሪካው ቡድን ለችግሩ ዲፕሎማሲያዊ መፍትሔ ለመስጠት ቁርጠኛ ነኝ ብሏል።የኒጀር ጦር ቃል አቀባይ ሜጅ ኮሎኔል አማዱ አብድራማኔ እበሰጡት መግለጫ በባዙም ጤና ዙሪያ የተነሱት ስጋቶችን ውድቅ በማድረግ ሀኪም እንዲያያቸዉ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ቅዳሜ እለት ቺያኒ በመከላከያ ሃላፊው በጄኔራል ሙሳ ባርሙ የሚመራ የልዑካን ቡድን ወደ ጊኒ ዋና ከተማ ኮናክሪ ልከዋል፡፡መሪዎች ላደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል፡፡
በስምኦን ደረጄ