በደቡባዊ ሩሲያ ዳግስታን ግዛት በነዳጅ ማደያ ላይ በደረሰ የእሳት ቃጠሎ እና ፍንዳታ ቢያንስ 25 ሰዎች ሲሞቱ ሶስት ህጻናትን ጨምሮ በርካታ ሰዎች ቆስለዋል ሲል የሩሲያው ኢንተርፋክስ የዜና ወኪል የክልሉን የድንገተኛ አደጋ ህክምና ባለሙያዎች ጠቅሶ ዘግቧል። እሳቱ ትላንት ምሽት በካስፒያን ባህር ላይ በምትገኘው በዳግስታኒ ግዛት ዋና ከተማ ማካችካላ በሚገኘው የፍጥነት መንገድ ዳር ላይ በሚገኝ የመኪና ጥገና ሱቅ ላይ ተነስቶ በአቅራቢያው ወደሚገኝ የነዳጅ ማደያ መስፋፋቱን ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል።
ፍንዳታው ልክ እንደ ጦርነት ይመስል ነበር ሲል አንድ የዓይን እማኝ ለሮይተርስ የዜና ወኪል ተናግሯል። የተጎዱት ሰዎች ቁጥር ወደ 66 ከፍ ብሏል ከነዚህም ውስጥ 10 ያህሉ በአስጊ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ሪአይኤ የዜና ወኪል የሩሲያ ምክትል የጤና ሚኒስትር ቭላድሚር ፊሴንኮን ጠቅሶ ዘግቧል። ከቆሰሉት ውስጥ 13ቱ ህጻናት ናቸው።
ከባድ ጉዳት የደረሰባቸውን ወደ ሞስኮ ለማጓጓዝ አውሮፕላን ወደ ማካቻካላ ተልኳል ሲል የሩስያ የአደጋ ጊዜ ጉዳዮች ሚኒስቴር በቴሌግራም የመልእክት መተግበሪያ ላይ ገልጿል።እሳቱ በግምት 600 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ መዛመቱን የገለፀው ሚኒስቴሩ 260 የእሳት አደጋ ተከላካዮች መሰማራታቸውንም ገልጿል። የእሳት አደጋ ተከላካዮች እሳቱን ለማጥፋት ከሶስት ሰአት ተኩል በላይ ፈጅቷል።
በስምኦን ደረጄ