
ነርስ ሉሲ ሌቢ በአራስ ክፍል ውስጥ ሰባት ሕፃናትን በመግደሏ ጥፋተኛ ሆና ተገኝታለች፣ ይህም በዩናይትድ ኪንግደም እጅግ አሳዛኙ የህፃናት ተከታታይ ግድያ ተደርጎ ተወስዷል፡፡
ከሰኔ 2015 እስከ ሰኔ 2016 ባለው ጊዜ ውስጥ በ ቼስተር ሆስፒታል ውስጥ ሌሎች ስድስት ጨቅላዎችን ለመግደል መሞከሯን የክሱ መዝገብ ያትታል፡፡የ33 ዓመቷ ሉሲ ሌቢ፣ በእሷ እንክብካቤ ስር ያሉ ሕፃናትን አየር ወደ ደማቸው እና ሆዳቸው በመርፌ እንዲገባ ፣ ወተት ከልክ በላይ በመመገብ፣ በአካል በማጥቃት እና በኢንሱሊን በመመረዝ ጉዳት አድርሳለች ሲል በሰሜን እንግሊዝ የሚገኘው የማንቸስተር ክራውን ፍርድ ቤት የቀረበዉ የክስ መዝገብ ያሳያል።
ሌቢ ሆን ብላ ሁለት ሕጻናትን በተለይ በኢንሱሊን በመመረዝ ገድላለች፡፡ከዚህ ሁሉ ድርጊት በኃላ በቅርቡ በነበሩ የችሎት ሂደት ላይ ለመቅረብ ፈቃደኛ አልሆነችም።በነሀሴ 8 ከ76 ሰአታት ውይይት በኋላ በዳኞች የክሱ ዝርዝር ሲነበብ ሌቢ እንባውን ስታዘራ ታይታለች፡፡ሁለተኛው የችሎት ዉሎ ነሀሴ 11 ሲደረግ አንገቷን ደፍታ ስታለቅስ ታይታለች፡፡
ጮክ ብላ እያለቀሰች የክሱ ሂደት ትክክል ሊሆን አይችልም ስትል ብትደመጥም ህይወታቸዉን ያጡት የጨቅላዎቹ ቤተሰቦች በተመሳሳይ ሲያለቅሱ ተስተዉለዋል፡፡ዳኞች በስድስት ተጨማሪ የግድያ ሙከራዎች ላይ ብይን መስጠት አልቻሉም።አቃቤ ህግ የሆነው ኒኮላስ ጆንሰን ኬሲ በእነዚህ ቀሪ ስድስት ክሶች ላይ ድጋሚ የፍርድ ሂደት ይታይ እንደሆነ ለማወቅ ፍርድ ቤቱን 28 ቀናት ጠይቋል።
እኤአ በ1990 በሄሬፎርድ የተወለደችዉ ሌቢ የጆን እና ሱዛን ሌቢ ብቸኛ ልጅ ነች፡፡ ወላጆቿ አሁን በጡረታ ላይ ቢገኙም በችርቻሮ ንግድ እና በሂሳብ ያዥነት ሰርተዋል፡፡ሌቢ በአካባቢው በሚገኝ ትምህርት ከተማረች በኃላ በ2011 በቼስተር ዩኒቨርሲቲ የህፃናት ነርስ በሚል ዘርፍ ተመርቃለች፡፡22ኛ ዓመት የልደት በዓሏን ልታከብር ሁለት ቀናት ሲቀሯት በካዉንትስ ቼስተር ሆስፒታል የማዋለጃ ክፍል ዉስጥ ተቀላቅላለች፡፡በሊቨርፑል የሴቶች ሆስፒታል የሥልጠና ምደባን አጠናቃለች፡፡
በምርመራው ወቅት ፖሊሶች የሌቢን ቤት ሲፈትሹ በእጅ የተጻፉ በርካታ ማስታወሻዎች አግኝተዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል “ይህን ያደረኩት ክፉ ስለሆንኩ” የሚለውን ጨምሮ በርካታ ማስረጃ ተገኝቷል።
በስምኦን ደረጄ