መደበኛ ያልሆነ

ነሐሴ 15፤2015-ኢትዮጲያ ከሻይ ቅጠል ሽያጭ ከ2 ሚሊዮን በላይ የአሜሪካን ዶላር ገቢ አገኘች

ኢትዮጵያ በዘንድሮው በጀት ዓመት ከሻይ ቅጠል ምርት ሽያጭ  ከ2 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ስለማግኘቷ የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለስልጣን አስታውቋል

የባለስልጣኑ  ዋና ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር  አዱኛ ደበላ ለብስራት ሬዲዮና ቲቪ እንደገለጹት  ይህ ገቢ ሊገኝ የቻለው 9 መቶ 22  ቶን የሻይ ቅጠል ምርት ለጨረታ ወደ ሚቀርበበት  ኬኒያ ሞምባሳ ወደብ በመላክ ነው፡፡

አያይዘውም በ2015 በጀት ዓመት የሻይ ምርትን ወደ ውጪ ሃገራት በመላክ ከ2 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር በላይ ገቢ ቢገኝም  3 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር ገቢ ለማግኘት እቅድ ተይዞ እንደነበር ገልጸዋል፡፡

የሀገር ውስጥ የሻይ ፍላጎት መጨመር እንዲሁም በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ ካሉ የሻይ ቅጠል አምራች ድርጅቶች መካከል አንዱ የሆነው ሆራይዘን ፕላንቴሽን የሻይ ቅጠል አምራች ድርጅት ብቻ የሻይ ቅጠል ምርትን ኤክስፖርት በማድረጉ በታቀደው ልክ ውጤት ማምጣት እንዳልተቻለ ተመላክቷል፡፡

አፈጻጸሙ ከባለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር በመጠንና  በገቢ  ጭማሪ ማሳየቱን  ዋና ዳይሬክተሩ ገልጸው አምና 9 መቶ 2.8 ቶን የሻይ ቅጠል ምርት  ኤክስፖርት ተደርጎ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

በገቢ ደረጃ 1.86 ሚሊዮን የአሜሪካን ዶላር  አምና ተገኝቶ እንደነበር ተገልጿል፡፡

በቅድስት ደጀኔ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *