መደበኛ ያልሆነ

ነሐሴ 15፤2015-የኤሌክትሪካል እና የባዮ ሜዲካል ኢንጅነሩ በስራ ላይ እያሉ በኤሌክትሪክ አደጋ ሕይወታቸው አለፈ

የአርማወር ሃንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት የኤሌክትሪክ እና ባዮ ሜዲካል ኢንጅነር የነበሩት አቶ ሽብሩ ደበላ በስራ ላይ እያሉ በኤሌትሪክ ድንገተኛ አደጋ  ህይወታቸው ማለፉን ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል፡፡

የኢንስቲትዩቱ የሕዝብ ግንኙነት እና የኮምንኬሽን ዳይሬክተር ደጅይጥኑ ሙላው ለብስራት ሬድየ እና ቴሌቪዥን እንደተናገሩት ፤ የኤሌክትሪክ እና ባዮ ሜዲካል ኢንጅነር የነበሩት አቶ ሽብሩ ደበላ እድሜያቸዉ 40 አመት የሚገመት ሲሆን ባለትዳር እና የሶስት ልጆች አባት ነበሩ፡፡

የኤሌክትሪክ እና ባዮ ሜዲካል ኢንጅነሩ አቶ ሽብሩ ደበላ የአርማወር ሃንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ሰራተኛ ከመሆናቸው አስቀድሞ የጅማ ዩንቨርስቲ መምህር እና ተመራማሪ እንደነበሩም ተነግሯል፡፡

ባለሙያው ወደ አርማወር ሃንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት ከተቀላቀሉ በኃላ በርካታ ስራዎች የሰሩ ሲሆን በተለይ ኢንስቲትዩቱ በእድሜ የገፋ እነደመሆኑ በርካታ የተበላሹ የምርምር ማሽኖች እንደነበሩት ያስታወቁት የኮምንኬሽን ዳይሬክተሯ ደጅይጥኑ ሙላው ፤ የኤሌክትሪክ እና ባዮ ሜዲካል ኢንጅነሩ አቶ ሽብሩ ደበላ ሊጣሉ የነበሩ እና አያገለግሉም ተብለው የተተው ማሽኖችን የሰሩና እና ዳግም ወደ ስራ ያስገቡ መሆናቸዉን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ በቁጥር አነስተኛ ከሆኑት የኤሌክትሪክ እና ባዮ ሜዲካል ኢንጅነሮችም አንዱ የሆኑት አቶ ሽብሩን ማጣት እንደ ኢንስቲትዩቱ ብቻ ሳይሆን እንደሀገርም ታላቅ ባለሙያ ማጣት ነው ተብላል፡፡

ባለሙያውም ህይወቱ ያለፈው በትርፍ ቀኑ ስራ ገብቶ ማሽኖችን በመጠገን ላይ እያለ ኤሌክትሪክ አደጋ  አጋጥሞት እናደነበር ብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ለማወቅ ችሏል፡፡

የኤሌክትሪክ እና ባዮ ሜዲካል ኢንጅነር የነበሩት አቶ ሽብሩ ደበላ በስራ ላይ እያሉ በደረሰባቸው ድንገተኛ አደጋ  ህይወታቸው በማለፉ  የአርማወር ሃንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት አመራሮችና ሰራተኞች እና የተሰማቸውን ልባዊ ሀዘን ገልጸዋል ።

የአርማወር ሃንሰን የምርምር ኢንስቲትዩት በስራ ላይ ህይወታቸው ላለፈው ባለሙያው ሙሉ ኢንሹራንስ እናደሚሰጥም ለማወቅ ችለናል፡፡

በትግስት ላቀዉ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *