መደበኛ ያልሆነ

ነሐሴ 16፤2015-በዉሃ ዳር በመዝናናት ላይ እያለች የጠፋችዉ የሐዋሳ ዩኒቨርስቲ ተማሪ አስክሬኗ ከሁለት ወራት ፍለጋ በኋላ 80 ኪ.ሜ ርቆ ተገኘ

በ 2015 ዓ.ም በሐዋሳ ዩኒቨርስቲ በንሳዳዬ ካምፓስ አዲስገቢ የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪ የነበረችዉ ኤደን ሙሉቀን ሰኔ 15 ቀን 2015 ዓ.ም የአንድ ጓደኛቸዉን ልደት ለማክበር ብሎም የማስታወሻ ፎቶግራፍ ለመነሳት በሚል በአካባቢው ወዳለ ገርጃ ወደተሰኘ ወንዝ 9 ተማሪዎች በአንድላይ ያቀናሉ።

የ 20 አመት ወጣት የነበረችዉ ኤደን በድንገት ከአንድ ጓደኛዋ ጋር ተንሸራትተዉ ዉሃዉ ይወስዳቸዋል። የኤደን ወላጅ አባት የሆኑት አቶ ሙሉቀን ደርቤ ለብስራት ራዲዮ እንደተናገሩት ፤ ያለፉትን ሁለት ወራት ልጃቸዉን በተለያዩ መንገዶች ሲፈልጉ እንደነበር ገልጸዋል። ሆኖም በወራጅ ወንዝ መወሰዷን ተከትሎ በህይወት የመገኘቷ እድል ጠባብ በመሆኑ ከሁለት ሳምንት ፍለጋ በኋላ ቤተሰብ ሀዘን ተቀምጦ እንደበር አስረድተዋል።

ሆኖም የሐዋሳ ዩኒቨርስቲ ፤ የአዲስአበባ እሳት አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ዋናተኞችን በማስመጣት ላለፉት ሁለት ወራት የተማሪዉን አስክሬን ሲያፈላልግ መቆየቱን ተናግረዋል። ወራትን የፈጀዉ የተማሪዋ ፍለጋ በስተመጨረሻ አደጋዉ ከተከሰተበት 80 ኪ.ሜትሮችን ርቆ አስክሬኗ በትናንትናው እለት መገኘቱን ለጣቢያችን ተናግረዋል።

በእለቱ ተማሪዎቹ ባጋጠማቸው አደጋ ቁጥራቸው አራት የሆኑ ተማሪዎች በወንዙ የተወሰዱ ሲሆን ሁለት ተማሪዎች ከአደጋዉ ተርፈዉ ነበር። ከኤደን ጋር አንድ ሌላ ወንድ ተማሪ በወንዙ የተወሰደ ሲሆን በተማሪዎች ርብርብ ማዳን ተችሎ የነበረ ቢሆንም ከቆይታ በኋላ ህይወቱ ማለፉን ጣቢያችን ሰምቷል።

የገናሌ ወንዝ ገባር በሆነዉ ገርጃ ወንዝ ላይ ጠፍታ የነበረችዉ ተማሪ ኤደን አስክሬኗን ከሁለት ወራት በኋላ የአዲስአበባ እሳት አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ዋናተኞች እንዳገኙት ነዉ የተማሪ ኤደን ወላጅ አባት አቶ ሙሉቀን ደርቤ ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን የተናገሩት።

በዛሬዉ እለትም በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደብረሊባኖስ ወረዳ ቃሲም ቀበሌ ቃሲም ስላሴ ቤተክርስቲያን የቀብር ስነስርዓቷ ቤተሰቦቿ እና የአካባቢው ማህበረሰብ በተገኘበት መፈጸሙን ብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ሰምቷል።

በበረከት ሞገስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *