መደበኛ ያልሆነ

ነሐሴ 16፤2015-ከ970 ሺ ብር በላይ ለግል ጥቅሟ ያዋለች የፋይናንስ ጽህፈት ቤት ኃላፊ በእስራትና በገንዘብ ተቀጣች

በቤንች ሸኮ ዞን በሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር  ከ970 ሺ ብር በላይ ለግል ጥቅሟ ያዋለች የአስተዳደሩ ፋይናንስ ጽህፈት ቤት ምክትል ሀላፊ በከባድ የእምነት ማጉደል ወንጀል ክስ የ10 ዓመት ጽኑ እስራትና የ15 ሺህ ብር የገንዘብ ቅጣት ተላልፎባታል ፡፡

ተከሳሽ ወ/ሮ ወርቅነሽ ተክሌ የሚዛን አማን ከተማ አስተዳደር ፋይናንስ ጽህፈት ቤት ምክትል ሃላፊ በመሆን ስታገለግል በነበረችበት ወቅት ከ2012 እስከ 2014 ዓ.ም ድረስ በእጇ የገባን ብር 970 ሺህ 356 ከ22 ሳንቲም ለግል ጥቅሟ ማዋሏ ተገልጿል ።

ሆኖም ገንዘቡን እንድትመልስ ስትጠየቅ መክፈል ስላልቻለች ክስ እንደተመሰረተባት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት እና ገፅታ ግንባታ ሀላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ደጀኔ አሰፋ ለብስራት ራዲዮና ቴልቪዥን ተናግረዋል ፡፡

ስለሆነም ተከሳሽ ወ/ሮ ወርቅነሽ ተክሌ በፈፀመችዉ ወንጄል በከባድ እምነት ማጉደል ተጠርጥራ በቤንች ሸኮ ዞን ፖሊስ መምሪያ የምርመራ መዝገብ ተጣርቶ የዞኑ ዐቃቢ ህግ ለቤንች ሸኮ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሰዉና የሰነድ ማስረጃ ማቅረቡ ተገልጿል ።

በዚህ መሠረት ተከሳሽ ወ/ሮ ወርቅነሽ ተክሌን የቤንች ሸኮ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ጥፋተኛ በማለት በ10 ዓመት ጽኑ እስራት እና በ15 ሺህ ብር የገንዘብ መቀጮ እንድትቀጣ ውሳኔ አስተላልፏል ፡፡

በአበረ ስሜነህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *