
የሊቢያ ጠቅላይ ሚኒስትር የሀገሪቱ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሯ ከእስራኤል አቻቸው ጋር መደበኛ ባልሆነ መንገድ ከተገናኙ በኋላ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯን ከስራ አግደዋል።
ሊቢያ የፍልስጤም ጠንካራ ደጋፊ ስትሆን ለእስራኤል እንደ ሀገግ እውቅና አልሰጠችም። የሚኒስትሯ መደበኛ ያልሆነ ስብሰባ በአብዛኛዎቹ የአረብ ሀገራት ተቃውሞ አስነስቷል። የእስራኤሉ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ኤሊ ኮኸን ከሊቢያ አቻቸው ናጃላ አል ማንጉሽ ጋር የተደረገው ስብሰባ የሀገራቱን ግንኙነት ለመመስረት ታሪካዊ የመጀመሪያ እርምጃ ነው ብለዋል።
እስራኤል በይፋ እውቅና ከማይሰጧት የአረብ ሀገራት ጋር የጠበቀ ግንኙነት ለመፍጠር እየሰራች ነው። ሆኖም የሶስቱን ግዛቶች የሚወክለው የሊቢያ ፕሬዚዳንታዊ ምክር ቤት ከእስራኤል ጋር ያለውን ግንኙነት መደበኛ ማድረግ ህገወጥ ነው ብሏል።
የፓርላማው አፈ ጉባኤ ፅህፈት ቤት የውጪ ገዳይ ሚኒስትሯን ወይዘሮ ማንጉሽ በትልቅ የሀገር ክህደት ወንጀል የከሰሷቻው ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱልሃሚድ ዲቤባህ ምርመራ እንዲደረግባት ትዕዛዝ ሰጥተዋል።በቀድሞው የሊቢያ መሪ ሙአመር ጋዳፊ ዘመን ሊቢያ የእስራኤል ዋንኛ ተቃዋሚ ስትሆን የፍልስጤም ትግል አቀንቃኝ በመሆና ከእስራኤል ጋር ድርድር አደረገች መባሉ አስገራሚ ነበር።
በጋዳፊ አገዛዝ ዘመ በሺዎች የሚቆጠሩ አይሁዶች ከሊቢያ የተባረሩ ሲሆን በርካታ ምኩራቦች ወድመዋል። የሊቢያ መንግስት ውጥረት ሲበዛበት በሚኒስትሯ ላይ ለማላከክ ፈልጎ እንጂ የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ታጃኒ በሁለቱ ሀገራት መካከል የሚደረገውን ውይትት በሮም ለማዘጋጀት እውቅና ሰጥተው ነበር።
በትላንትናው እለት አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የእስራኤል መንግስት ባለስልጣን ለሮይተርስ የዜና ወኪል እንደተናገሩት ስብሰባው በሊቢያ በከፍተኛ ደረጃ ለማድረግ አስቀድሞ ስምምነት ላይ የተደረሰ እና ከአንድ ሰአት በላይ የፈጀ ውይይት መደረጉን ገልፀዋል።ሚስተር ኮኸን በሰጡት መግለጫ ባለፈው ሳምንት በሮም በተካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ከወ/ሮ ማንጉሽ ጋር እንደተገናኙ እና በእስራኤል እና በሊቢያ መካከል ስላለው ግንኙነት ትልቅ መወያየታቸውን ተናግረዋል ።
በሰብአዊ መብት ጉዳዮች፣ በግብርና፣ በውሃ አያያዝ እና በሊቢያ የአይሁድ ቅርሶችን ስለመጠበቅ አስፈላጊነት፣ ምኩራቦችን እና የመቃብር ቦታዎችን በማደስ ዙሪያ የእስራኤል እርዳታ በተመለከተ መነጋገራቸውን ተናግረዋል።የስብሰባውን ዜና ተከትሎ በዋና ከተማዋ ትሪፖሊ እና በአንዳንድ ከተሞች ተቃውሞ ተቀስቅሷል።
መንገዶች ተዘግተዋል፣ ጎማዎች ተቃጥለዋል እና ሰልፈኞች የፍልስጤምን ባንዲራ አውለብልበዋል።
በስምኦን ደረጄ