መደበኛ ያልሆነ

ነሐሴ 24፤2015-ጠቅላይ ሚኒስትር ኔታንያሁ በድንገተኛ ሁኔታ እስራኤላውያኑን ያሳፈረው አውሮፕላን ካረፈ በኃላ ሳዑዲ አረቢያን አመሰገኑ

እስራኤላውያንን ከህንድ ውቅያኖስ የደሴት ሀገር ሲሸልስ ወደ እስራኤል ያሳፈረው አውሮፕላን መዳረሻውን ቴል አቪቭ ከተማ ላይ ከማድረጉ በፊት በሳውዲ አረቢያ በድንገተኛ ለማረፍ ተገዷል። እስራኤል በሁለቱ ሀገራት መካከል መደበኛ ግንኙነት ለመመስረት እየሰራች ባለችበት በዚህ ወቅት የመልካም ምኞት ምልክት ነው በማለት ሳዑዲ አውሮፕላኑ እንዲያርፍ በመፍቀዷ አሞካሽታለች።

አውሮፕላኑ ቴል አቪቭ ላይ ካረፈ በኋላ፣ ከሳዑዲ አረቢያ ጋር ግንኙነት መመስረት ትልቅ ግብ ነው ያሉት የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ድርጊቱ ግንኙነታቸውን ለማሻሻል ያለውን አቅም አጉልቶ አሳይቷል ብለዋል። “የሳውዲ ባለስልጣናት በበረራ ወቅት በተፈጠረ ድንገተኛ ችግር በጭንቀት ላይ ለነበሩት እስራኤላውያን መንገደኞች ያላቸውን መልካም አመለካከት በጣም አደንቃለሁ” ሲሉ ኔታንያሁ በዕብራይስጥ በተቀረጸ ቪዲዮ እና በአረብኛ የትርጉም ጽሑፍ መልዕክታቸውን አጋርተዋል።

አክለውም “መልካም ጉርብትናን በጣም አደንቃለሁ” ሲሉ ተናግረዋል። 128 መንገደኞችን አሳፍሮ የነበረው የኤር ሲሸልስ በረራ ሰኞ ዕለት በኤሌክትሪክ ችግር ምክንያት ለማረፍ ተገዷል። የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ተሳፋሪዎቹ ሌሊቱን በጅዳ በሚገኘው አየር ማረፊያ ሆቴል ያረፉ ሲሆን በተለዋጭ አውሮፕላን ወደ እስራኤል እንዲመለሱ ተደርጓል።

የበረራ ክትትል መረጃ እንደሚያሳየው የሲሸልስ አየር መንገድ ንብረት የሆነው ኤርባስ ኤ 320 በረራ ቁጥሩ ኤችኤም22 ሰኞ ምሽት በቀይ ባህር ላይ እያለ ወደ ጅዳ መስመር መቀየሩን ያሳያል። አየር መንገዱ በጉዳዩ ላይ እስካሁን ድረስ አስተያየት አልሰጠም።

በስምኦን ደረጄ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *