
የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፈታህ አል ሲሲ ሀገሪቱ አደጋ እንዳይደርስባት የወሊድ ምጣኔን መቀነስ አለባት ብለዋል።
ግብፅ ለዜጎቿ የስራ እና ማህበራዊ አገልግሎቶችን በብቃት ለማቅረብ አሁን ካለበት ዓመታዊ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የውልደት ምጣኔ ወደ 400,000 ዝቅ ማድረግ አለባት ሲሉ ፕሬዝዳንት አል ሲሲ ገልፀዋል። በግብፅ በየዓመቱ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ህፃናት እንደሚወለዱ መረጃዎች ያሳያሉ።
ፕሬዝዳንት አል-ሲሲ አክለው የግብፅ የጤና እና የህዝብ ቁጥር ሚኒስትር ካሊድ አብደል ጋፋር “ልጆች መውለድ ፍፁም ነፃነት ጉዳይ ነው” የሚለውን ሀሳብ ማንሳታቸው ስህተት ነው ሲሉ አክለዋልበመጀመርያው የዓለም የሕዝብ፣ ጤና እና ልማት ጉባኤ ላይ ፕሬዝዳንቱ ባደረጉት ንግግር ነፃነትን ሊያመጣ ስለሚችለው ችግር ለማያውቁ ሰዎች መተው በመጨረሻ የሚያስከትለውን ዋጋ የሚከፍለው መላው ህብረተሰብ እና የግብፅ መንግስት ናቸው ብለዋል ።
“ይህን ነፃነት ማደራጀት አለብን ይህ ካልሆነ ግን ጥፋት ይፈጥራል” ሲሉም አክለዋል። ቻይና “በሕዝብ ቁጥጥር ፖሊሲዋ ተሳክቶላታል ” ያሉት ፕሬዝዳንቱ ግብፅ የቻይናን የአንድ ልጅ ፖሊሲ ልትኮርጅ እንደምትችል ፍንጭ ሰጥተዋል።
እ.ኤ.አ ከ2000 ጀምሮ በአፍሪካ ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት አላቸው ከሚባሉ ሀገራት መካከል አንዷ የሆነችው ግብፅ ባለፉት 23 ዓመታት የሕዝቧ ብዛት በ40 ሚሊዮን ጨምሯል። ዛሬ ላይ የግብፅ ህዝብ ብዛት 105 ሚሊዮን መድረሱን አብደልጋፋር ተናግረዋል።
በአፍሪካ እየጨመረ ለሚሄደው ህዝብ በቂ ሃብት ስለሌለ ሀገራት የህዝብ ቁጥር መቆጣጠሪያ እርምጃዎችን መውሰድ አለባቸው ሲሉ ፕሬዝዳብት አል ሲሲ ተናግረዋል።
በስምኦን ደረጄ