
በሱዳን ዋና ከተማ በጦር ኃይሉ እና በተፋላሚ ሃይሎች መካከል ከፍተኛ ጦርነት ከተፈጠረ በኋላ ሕንፃዎች ሲቃጠሉ ታይተዋል።በትላንትናው እለት በተሰራጩ ቪዲዮዎች መሰረት የታላቁ ናይል ፔትሮሊየም ኦይል ኩባንያ ታወር በእሳት ጋይቷል።
የሕንፃው መሐንዲስ ታግሬድ አብዲን ቀደም ሲል ትዊተር ተብሎ በሚጠራው በአሁኑ ኤክስ ላይ በለጠፉት ጽሑፍ “ይህ በእውነት በጣም ያማል ሲሉ አጋርተዋል። ጦርነቱ በሚያዝያ ወር ከተቀሰቀሰ በኋላ በካርቱም እና በሌሎች ከተሞች የአየር ድብደባ እና የምድር ጦርነቶች ቀጥለዋል። ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሀገሪቱን ለቀው ለመሰደድ መገደዳቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አስታውቋል።
በናይል ወንዝ አቅራቢያ የሚገኘው ባለ 18 ፎቅ የነዳጅ ኩባንያ ሰማይ ጠቀስ ህንጻ በካርቱም ውስጥ በጣም ከሚታወቁ የከተማዋ ምልክቶች አንዱ ነው። ወይዘሮ ታግሬድ አብዲ የከተማዋን ገጽታ እንደሚገልፅ ተናግረው “እንዲህ ያለ ትርጉም የለሽ ውድመት” ያስቆጫል ስትል ተናግራለች። በመስታወት የተሸፈነው የሕንፃው ሾጣጣ መሰል መዋቅር በእሳት የተቃጠለበት ምክንያት ምን እንደሆነ እስካሁን አልታወቀም። በደረሰው ውድመት በሰው ላይ የአካል ጉዳትም ሆነ ሞት አልተመዘገበም።
በሱዳን ያለው ጦርነት የጀመረው በሚያዚያ አጋማሽ በሱዳን ጦር መሪዎች እና በፓራሚትሪ የፈጣን ድጋፍ ሰጭ ሃይሎችመካከል በተፈጠረ የስልጣን ሽኩቻ እንደነበር ይታወሳል። የግጭት ትንተናን የሚያቀርበው የሱዳን ዋር ሞኒተር በበኩሉ አርኤስኤፍ ቅዳሜ ዕለት በፍትህ ሚኒስቴር ውስጥ የሚገኘውን ፅህፈት ቤት ጨምሮ በሰራዊቱ ቁጥጥር ስር ያሉ ቦታዎች ላይ ጥቃት ማድረሱን ገልጿል። በጥቃቱ ምክንያት በርካታ የመንግስት ህንጻዎች መቃጠላቸው ተዘግቧል።
በከተማዋ ደቡባዊ ወረዳ የሚኖሩ ነዋሪዎች ሰራዊቱ የአር ኤስ ኤፍ ጦር ሰፈሮችን ኢላማ ያደረገበትን ጥቃት ከእንቅልፋቸው ሲነቁ “ትልቅ ድብደባ” እንደሰሙ ለኤኤፍፒ ተናግረዋል። የጤና ባለስልጣናት እሁድ እለት በካርቱም የሚገኙ ዋና ዋና ሆስፒታሎች እንዲሁም የዳርፉር ክልል ከአገልግሎት ውጪ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ከካርቱም በስተደቡብ 400 ኪሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ኤል-ኦበይድ ከተማ ከባድ ውጊያ መካሄዱ ታውቋል። አርኤስኤፍ ዋና ከተማዋን ለመቆጣጠር ሲታገል የቆየ ሲሆን ወታደራዊ ኃይሉ በበኩሉ በአርኤስኤፍ ይዞታዎች ላይ የአየር ጥቃት በመፈፀም ቡድኑን ለማዳከም ያለመ እንቅስቃሴ እያደረገ መሆኑን ያሳያል።
በግጭቱ ወደ 7,500 የሚጠጉ ሰዎች እስካሁን የተገደሉ ሲሆን ከአምስት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከመኖሪያ ስፍራቸው ተፈናቅለዋል።
በስምኦን ደረጄ