መደበኛ ያልሆነ

መስከረም 7፤2016-ደቡብ አፍሪካ በውሃ እጥረት የተነሳ ዜጎቿ ለሁለት ደቂቃ ያህል ብቻ ሻወር እንዲወስዱ መከረች

በደቡብ አፍሪካ ጆሃንስበርግ የሚገኙ የውሃ አቅራቢዎች የከተማዋ ነዋሪዎች እና የከተማዋ ዳርቻዎች የውሃ እጥረት እየተባባሰ በመምጣቱ አነስተኛ ውሃ እንዲጠቀሙ ጠይቀዋል።

ይህንን ዜጎች ማድረግ ካልቻሉ የውሃ ስርዓቱ ላይ መላውን ውድቀት ሊያስከትል ይችላል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።የራንድ እና የጆሃንስበርግ ውሃ አስተዳደር እንዳስታወቁት በነዋሪዎች ከፍተኛ የውሃ ፍጆታ የተነሳ “በስርዓቱ ላይ ጫና እየፈጠረ ነው” እናም የውሃ ማጠራቀሚያ ደረጃ በጣም ዝቅተኛ እንዲሆን አድርጓል ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

ኩባንያዎቹ ነዋሪዎች ውሃ እንዲቆጥቡ በማለት ሻወር ውስጥ ለሁለት ደቂቃ ብቻ እንዲቆዩ፣ መጸዳጃ ቤቶችን ብቻ እንዲያጥቡ በተጨማሪም ቅዳሜና እሁድ ብቻ መኪናዎችን በባልዲ በመጠቀም ብቻ ማጠብ እንደሚኖርባቸው ገልፀዋል። ኩባንያዎቹ የውሃ እጥረት እስኪያበቃ ድረስ የመዋኛ ገንዳዎችን ውሃ ለመሙላት እንዲቆጠቡ፣ አትክልቶችን እና የሣር ሜዳዎችን በንፁህ ውሃ ከማጠጣት እንዲያቆሙ እንዲሁም የውሃ ፍሳሽ መስመሮች ላይ ማንጠባጠብ ካለ እንዲያስተካክሉ ወይም እንዲጠቁሙ ጠይቀዋል።

በጆሃንስበርግ ይህ ወቅት አመታዊ የውሃ ገደብ የምትጥልበት ነው።ይህም ብዙውን ጊዜ በደቡብ አፍሪካ ደረቅ ወቅት የሚባለው ከመስከረም እስከ መጋቢት መካከል ባሉት ወራቶች ውስጥ ይቆያል።ባለፉት ሳምንታት አንዳንድ የከተማዋ ነዋሪዎች እና እንደ ሆስፒታሎች ያሉ ተቋማት ውሃ አጥተው በህዝቡ ቅሬታ ፈጥረዋል።

ለዓመታት ደቡብ አፍሪካውያን የዕለት ተዕለት ኑሮን በእጅጉ የሚጎዳውን የውሃ ችግር ተቋቁመዋል። የአየር ንብረት ለውጥ ነገሮችን እያባባሰ ነው። ነገር ግን የውሃ እጥረቱ በዋናነት በሰዎች ድርጊት አስከፊ ውጤቶች ምክንያት እየተባባሰ ሲሆን ለውሃ መስመር በቂ ጥገና አለማድረግ ብክነት እንዲጨምር እና እጥረት እንዲፈጠር አድርጓል።

በስምኦን ደረጄ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *