መደበኛ ያልሆነ

መስከረም 9፤2016-በአዲስ አበባ ከተማ ጎዳናዎች ላይ ሽንት መሽናትን ያስቀራል የተባለ መመሪያ በ2016 ዓመት ይጸድቃል ተባለ

በአዲስ አበባ ከተማ በየመንገዱ እና በጎዳና ላይ የሚደረግ መጸዳዳት አስነዋሪ ተግባር መሆኑ ቀርቶ የከተማዋ መገለጫ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ ችግሩን ለማስቀረት መመሪያ መዘጋጀቱን  የከተማ ልማትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ አስታዉቋል፡፡

በቢሮው የአረንጓዴ አካባቢዎች አያያዝ ክትትል ቁጥጥር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ አጥናፏ እንዲህ ያለ ድርጊትን በሚፈጽሙት ሰዎች ላይ አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ እየሰራን ነው ሲሉ ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።ከዚህ ቀደም በነበሩት የአሰራር ደንቦች ላይ ማስተካከያ ለማድረግ ታስቦ መመሪያው መዘጋጀቱን ገልፃዋል።

በዚሁ መመሪያ ላይ አስተማሪ የሆኑ ቅጣቶች እንዲተገበሩ ታቅዷል ሲሉ አክለዋል።አያይዘው በከተማዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከመጣው የህዝብ ቁጥር አንጻር ሰፊ እንቅስቃሴ የሚደረግ በመሆኑ የከተማዋን ገጽታ በማበላሸት ድርጊቱ ጎጂ በመሆኑ የመመሪያው መጽደቅ ይህንን ችግር ሊቀርፍ ይችላል ብለዋል፡፡

በአዲስ አበባ እለት ተእለት የሚስተዋለውን የጎዳና ላይ መጸዳዳት ችግርን ለማስቀረት ያግዛል የተባለው ይኸው መመሪያ በቅርቡ ወደ ፍትህ ቢሮ ተልኮ  በዚህ አመት እንዲጸድቅ ይደረጋል  ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በቅድስት ደጀኔ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *