መደበኛ ያልሆነ

ጥቅምት 9፤2016 – ከስጋ መጥበሻ ላይ በተነሳ የእሳት አደጋ ከ1.5 ሚሊየን ብር የሚገመት ንብረት ወደመ

የእሳት አደጋው የደረሰው  ትላንት ጥቅምት 8 ቀን 2016 ዓ.ም ከምሽቱ 4:40 ሰዓት በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ብራስ አካባቢ በሚገኘው በፉድ ዞን ሆቴል መሆኑን የእሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን አስታውቋል።

የኮሚሽኑ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ንጋቱ ማሞ ለብስራት ሬድዮ እና ቴሌቭዥን እንደተናገሩት የእሳት አደጋዉ በሆቴሉ ከምግብ ማብሰያ ክፍል ዉስጥ ከስጋ መጥበሻ ሲሆን በአደጋው 1ነጥብ 5 ሚሊየን ብር የተገመተ ንብረት ወድማል።

የእሳት አደጋዉን ለመቆጣጠር አራት የአደጋ መቆጣጠር ተሽከርካሪ ከሀያ አምስት የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች ጋር የተሰማሩ ሲሆን የእሳት አደጋዉ ተዛምቶ ተጨማሪ ጉዳት ሳያደርስ ለመቆጣጠር የተቻለ ሲሆን በዚህ ሂደትም 11 ሚሊየን ብር የተገመተ ንብረት ማዳን መቻሉን አቶ ንጋቱ ጨምረው ተናግረዋል።

በእሳት አደጋዉ በሰዉ ላይ ጉዳት ያልደረሰ ሲሆን አደጋዉን ለመቆጣጠርም 1:31 ሰዓት ፈጅቷል።በሌላ በኩል ትላንት ከቀኑ 9:49 ሰዓት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ፒኮክ መናፈሻ በደረሰዉ የእሳት አደጋ በአንድ መኖሪያ ቤት ላይ ጉዳት ደርሷል።

በአዲስ አበባ የክረምት ጊዜ መጠናቀቁን ተከትሎ የእሳት አደጋ እየተደጋገመ መምጣቱን ኮሚሽኑ አስታውቃል።አሁን ያለንበት የአየር ጸባይ ለእሳት አደጋ መከሰትና መባባስ አስተዋጽኦ ያለዉ በመሆኑ ህብረተሰቡ ከወትሮዉ የተለየ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ኮሚሽኑ አሳስቧል።

በስምኦን ደረጄ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *