መደበኛ ያልሆነ

ጥቅምት 29፤2016 –በጂማ ከተማ በሞባይል ባንኪንግ ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ የማጭበርበር ወንጀል የፈጸሙ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

በጅማ ከተማ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች የሿሿ ስርቆት ሲፈጽሙ የነበሩት ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር  ስር መዋላቸውን  የጅማ ከተማ ፖሊስ ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት አስታውቋል።

አንደኛ ተከሳሽ ነብዪ ጭሌ ነዋሪነቱ ወልቂጤ ከተማ  ሲሆን ሁለተኛ ተከሳሽ ታምራት አማረ  ነዋሪነቱ በሃዋሳ ከተማ እንደሆነ መረጋገጡን የፅህፈት ቤቱ ኃላፊ ምክትል ኮማንደር ገዛኸኝ አውግቸው በተለይ ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል። ተከሳሾቹ የ30 ዓመቷን  ወጣት ከብሄራዊ ሎተሪ ዕጣ እንደደረሳቸው በመንገር  መታወቂ ስለሌላቸው ገንዘቡን መውሰድ አለመቻላቸውን  በመንገር እንዳታለሏት ተጠቁሟል።

በመሆኑም በሰዓቱ  እንደትተባበራቸው በመጠየቅ በተለምዶ ሿሿ የሚባለውን የወንጀል ድርጊት እንደፈፀሙባት ተመላክቷል። በዚህም በሞባይል ባንኪንግ  37 ሺህ ብር ፣ አንገቷ ላይ የነበረውን ወርቅ  እና  የእጅ ስልኳን ጨምሮ በአጠቃላይ 61 ሺህ ብር ንብረት ዘርፈው በባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪ ለማምለጥ ሞክረዋል  ።

ይሁን እንጂ የባጃጁ አሽከርካሪ ተከታትሎ በፖሊስ ቁጥጥር  ስር እንዲውሉ አድርጎል።  ግለሰቦቹ ሿሿ በተሰኘ የማታለል ተግባር  ስማቸውን እና አድራሻቸውን በመቀየር አዲስ አበባ  ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች ድርጊቱን ሲፈጽሙ መቆየታቸው ተረጋግጧል ።

አንደኛ ተከሰሽ ነብዩ ጭሌ  የተባለው ግለሰብ  አብዱሰላም ጀብል፣ አምዲ ከድር ፣ ኢማን ኑሩ በሚል የሀሰተኛ ስም ሲጠቀም ቆይቷል።በተመሳሳይ  ሁለተኛ ተከሳሽ ታምራት አማረ በሀሰተኛ ስም አሊ ጥላሁን በሚል ስያሜ  የተለያዩ ግለሰቦች ላይ የሞባይል ባንኪንግ  አማካኝነት ከ3 ሚሊየን ብር በላይ የማጭበርበር  ተግባር በመፈጸም በፖሊስ ሲፈለጉ የነበረ መሆኑንም ምክትል ኮማንደር ገዛኸኝ አውግቸው ጨምረው ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በኤደን ሽመልስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *