መደበኛ ያልሆነ

ጥቅምት 29፤2016 –የየመን አማጽያን የአሜሪካ ሰው አልባ አውሮፕላን ተኩሰው ጣሉ

የየመን የሁቲ አማፂያን ንብረትነቱ የዩናይትድ ስቴትስ የሆነ ወታደራዊ ሰው አልባ አውሮፕላን መተኮሳቸውን የአሜሪካ ባለስልጣናት እና ከኢራን ጋር የተቆራኙ የሁቲ እንቅስቃሴ ኃይሎች ተናግረዋል። የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣን እንዳስታወቁት ኤምኪው ዘጠኝ የተሰኘ ሰው አልባ ሰው አልባ አውሮፕላን በየመን የባህር ዳርቻ በሁቲ ሃይሎች ተመቷል ብለዋል። ተመሳሳዩ መረጃ በሁቲ ወታደራዊ ቃል አቀባይ ተረጋግጧል።

ባለፈው ወር የዩናይትድ ስቴትስ የባህር ኃይል የጦር መርከብ ሁቲዎች ከየመን ወደ እስራኤል ያስወነጨፉትን ክሩዝ ሚሳኤሎችን እና በርካታ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ጠልፏል።በእስራኤል እና በጋዛ ጦርነት ዙሪያ በተፈጠረው ቀጣናዊ ውጥረት የተነሳ ዩናይትድ ስቴትስ የአውሮፕላን ተሸካሚዎችን፣ የባህር ኃይል መርከቦችን እና የድጋፍ መርከቦችን ጨምሮ ወታደራዊ ንብረቶችን ወደ መካከለኛው ምስራቅ አስጠግታለች። በተጨማሪም ወታደሮቿ በየመን እና በእስራኤል መካከል ባለው ቀይ ባህር ውስጥ በወታደራዊ መርከቦች ላይ እንዲሰፍሩ ማድረጓ ይታወሳል።

የየመን ሁቲ አማፂያን በኢራን የሚደገፉ ሲሆን ከ2014 ጀምሮ በሳዑዲ አረቢያ ከሚደገፈው የሀዲ መንግስት ጋር ለረጅም ጊዜ የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ገብተዋል። በአካባቢው ያለው ሌላኛው በኢራን የሚደገፍ ቡድን የሊባኖሱ ሂዝቦላህ ምክትል መሪ በዚህ ሳምንት እንደተናገሩት እስራኤል በጋዛ በሰላማዊ ሰዎች ላይ የፈፀመችው ግድያ በመካከለኛው ምስራቅ ሰፋ ያለ ጦርነት ሊያስከትል ይችላል ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል። ሼክ ናይም ቃሴም እንዳሉት “በአካባቢው በጣም አሳሳቢ እና በጣም አደገኛ የሆኑ ክስተቶች ሊያጋጥም ይችላሉ፤ እናም ማንም ሰው መዘዞቹን ሊያስቆመው አይችልም” ብለዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ዩናይትድ ስቴትስ በምስራቅ ሶሪያ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ጥበቃ ጓድ እና አጋር ቡድኖች ይጠቀምበታል ባለችው ተቋም ላይ ጥቃት መፈፀሟን በትላንትናው እለት ተናግራለች።የፔንታጎን ባለስልጣን ጥቃቱ ባለፉት ሳምንታት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ የተካሄደ መሆኑን በማሳወቅ በዩናይትድ ስቴትስ የኢራቅ እና ሶሪያ የጦር ሰፈር ውስጥ ለደረሰው ጥቃት የአፀፋ ምላሽ ነው ብሏል። የሶሪያ የሰብአዊ መብት ታዛቢ ቡድን በበኩሉ ጥቃቱ በሶሪያ ውስጥ በኢራን ከሚደገፉ ቡድኖች ጋር ግንኙነት ያላቸውን ዘጠኝ ሰዎች መግደሉን ገልጿል፤ ይህ አሃዝ በሌላ አካል ግን ሊረጋገጥ አልቻለም።

በስምኦን ደረጄ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *