መደበኛ ያልሆነ

ህዳር 3፤2016-የህዳሴ ግድብ ሀይቅ አጎራባች በሆኑ ከተሞች ከፍተኛ የመሬት ወረራ እየተፈጸመ ነዉ ተባለ

???????? በተለይም በግልገል በለስ ከተማ ከፍ ያለ የመሬት ወረራ ተፈጽሟል

በታላቁ የህዳሴ ግድብ ዙሪያ በሚፈጠሩ ደሴቶች እና ቀድሞዉኑም በነበሩ ከተሞች ይፈጠራል ተብሎ የሚታሰበዉን ኢኮኖሚያዊ መነቃቃት ለመጠቀም ከፍተኛ የመሬት ወረራ መፈጸሙን እንዳስተዋለ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ አሳዉቋል።

የቢሮዉ ም/ል ሃላፊ ኢንጂነር ቢፍቱ ጎሹ ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን እንደተናገሩት ፤ በክልሉ ከግድቡ ግንባታ መጠናቀቅ በኋላ የሚፈጠረዉን ኢኮኖሚያዊ መነቃቃትን ለመጠቀም ከ 2013 ዓ.ም ጀምሮ ከፍተኛ የመሬት ወረራ መፈጸሙን ተናግረዋል። ላለፉት 3 አመታት ተፈሟል ካሉት የመሬት ወረራ ዉስጥ ከፍ ያለዉ በግድቡ አቅራቢያ በምትገኘዉ የግልገል በለስ ከተማ በሊዝ አዋጅ ጥሰት መፈጸሙን ገልጸዋል።

በከተማዉ ለተፈጸመዉ የመሬት ወረራ የከተማዉን የቀድሞ ከንቲባ እና በርካታ መሐንዲሶች በህግ ቁጥጥር ስር እንዲዉሉ መደረጉንም ጠቅሰዋል። በከተማዉ ከ 43 ሺህ ካሬ ሜትር በላይ መሬት ላይ ማጣራት ተደርጎ አብዛኛዉ በህገወጥ መንገድ ተወርሮ መገኘቱን አክለዋል። ቢሮዉ ህገወጥ ሰነዶች እንዲመክኑ ፤ አለአግባብ የተወሰደ መሬት እንዲመለስ ማድረጉንም ገልጸዋል። ከተማዋ ወደ ህዳሴ ግድብ ለሚደረግ ጉዞ እንደ ማረፊያ ቦታነት እንደምታገለግልም ተናግረዋል። በከተማዋ ዙሪያ ከነበረዉ የጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ አንዳንድ ሰዎች የድርሻቸዉን ወስደዉ ነበር ሲሉም የነበረዉን ሁኔታ ገልጸዉታል።

በተመሳሳይ አሶሳ ዙሪያ እና ባንባሲ ወረዳ እንዲሁም ካማሺ ዞን በተሰኙ አነስተኛ ከተሞችም በግልገል በለስ ከተማ ደረጃ ከመንግስት ባለስልጣናት እና ሰራተኞች ጋር በመረብ የተሳሰረ አይሁን እንጂ የመሬት ወረራዉ መታየቱን እና የመከላከል ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

በግድቡ ግንባታ ጋር ተያይዞ ከ 70 በላይ ከአነስተኛ እስከ ከፍተኛ ደሴቶች የሚፈጠሩ ሲሆን የቱሪስት መናኸሪያ እንደሚሆኑ ይጠበቃል። ይህንኑ ተከትሎ ለክልሉም ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እድገት አስተዋጽኦ የሚያበረክት ሲሆን ከዚሁ ኢኮኖሚያዊ መነቃቃት ጋር ተያይዞ ተጠቃሚ ለመሆን በሚል የመሬት ወረራ መፈጸሙን አስረድተዉናል።

የክልሉ ከተማና መሰረተ ልማት  ቢሮ  በሀገርአቀፍ ከተያዘዉ እቅድ ጎን ለጎን በግድቡ ዳርቻ የሚገኙ ከተሞች የሚመሩበትን ማስተር ፕላን እያዘጋጀ መሆኑንም ተናግረዋል። ይህም ከተሞች ከከተሞች የሚተሳሰሩበትን ሰፊ መንገዶች ፣ የመዝናኛ እና ሌሎች መስሕቦች የሚገናኙበትን መንገድ እየቀረጹ እንደሆነ7 አክለዋል።

በግድቡ ግንባታ ማንኩሽ ፣ ጎንቆሮ ፣ ሳድልዳሜ የተሰኙት ከተሞች ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ሊያገኙ ይችላሉ የተባለ ሲሆን የተለየ መነቃቃት እየታየባቸዉ መሆኑንም ገልጸዋል። የክልሉ ከተማ እና መሰረተ ልማት ቢሮ ቀሪ የአሰራር እና የደንብ ጥሰት የፈጸሙ ሰዎችን የህግ ተጠያቂ ያደርጋል ሲሉም ጨምረዉ ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በበረከት ሞገስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *