መደበኛ ያልሆነ

ህዳር 10፤2016 – በጓደኛቸው የስራ መሳካት በመቅናት የግድያ ወንጀል የፈፀሙ ግለሰቦች በእስራት ተቀጡ

እንዴት ከእኛ በተሻለ ስራ በለጥከን በማለት ጓደኛቸውን ደብድበው የገደሉት ተከሳሾች በእስራት መቀጣታቸውን የቦረና ዞን ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።

ተከሳሽ ቢሊሱማ ለገሰ፣  ቦሩ ቢቂላ ፣  ገና አለማየሁ ፣ቦሩ  ግልገሌ ፣ ሮባ ዲዳ  በህገወጥ ንግድ ላይ ተሰማርተው ሲንቀሳቀሱ እንደነበር በፖሊስ መምሪያው የወንጀል ምርመራ ክፍል ሃላፊ  ኢንስፔክተር አብዲ መሃመድ ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።ወጣቶቹ የኮንትሮባንድ ቁጥጥሩ እየጠነከረ መምጣቱን ተከትሎ  እንዴት መስራት እንዳለባቸው ሲወያዩ መቆየታቸው ተጠቁሟል።

ከእነዚህ ወጣቶች  መካከል  ሙሳ የተባለው ግለሰብ በተለየ መልኩ አየር በአየር ንግድ ሲሰራ ቆይቶ ከእነሱ በመለየት የልብስ እና የጫማ ንግድ ላይ መሰማራቱ ተነግሯል  ።   ተከሳሾች ከእነሱ ተለይቶ በመለወጡ  እና የተሻለ ስራ ላይ ለመሆኑ የኮንትሮባንድ ንግድ እንደጠቀመው ያስባሉ።

 በዚህም መጠጥ ቤት ቁጭ ብለው እየጠጡ ባለበት ቦሩ ቢቂላ ለጓደኞቹ እቃ አስጭኖ  በሞተር እንዳስባ በመንገር መዝረፍ እንደሚችሉ ይነግራቸዋል።አንደኛ እና አምስተኛ ተከሳሽ ስለታም የጦር መሳሪያ እና ቢላ በመያዝ   ፣  ሶስቱ  ተከሳሾች ሙሳ የተባለውን ግለሰብ ግምታቸው 78 ሺህ የሚሆን ጫማዎች  ጭኖ በሚሄድበት ሰዓት ወንጀሉን መፈጸማቸው ተረጋግጧል ።

ግለሰቡን በተደጋጋሚ በመምታት እና በስለት በመውጋት  ህይወቱ እንዳለፈ ካረጋገጡ በኋላ ንብረቱን ይዘው ተሰውረዋል።  በመሆኑም ፖሊስ ጉዳዩን አጣርቶ  እና የምርመራ መዝገቡን  በማጠናከር ለዓቃቢህግ ይልካል።

የቦረና ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክሱን ተመልክቶ  አምስቱ ግለሰቦች እያንዳንዳቸውን በ20 ዓመት እስራት እንዲቀጡ መወሰኑን  የቦረና ዞን ፖሊስ መምሪያ  የወንጀል ምርመራ ክፍል ሃላፊ  ኢንስፔክተር አብዲ መሃመድ ጨምረውም ለብስራት ሬዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

በኤደን ሽመልስ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *