መደበኛ ያልሆነ

ህዳር 14፤2016 – አሳድጋለሁ ብላ የወሰደቻትን ልጅ በመደብደብ ከባድ የአካል ጉዳት ያደረሰችው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ዋለች

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአሪ ዞን በጂንካ ከተማ አሳድጋለሁ ብላ ከቤተሰቦቿ የተቀበለቻትን የ13 ዓመት ልጅ በተደጋጋሚ በመደብደብና በማሰቃየት ከባድ የአካል ጉዳት ያደረሰች ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋሏ ተነግሯል ።

ወ/ሮ ታደለች ሲሳይ የተባለች ግለሰብ ከወላይታ ዞን ህጻን ተስፋነሽ ቡሳን አሳድጋለሁ እንዲሁም አስተምራታሁ በማለት ከቤተሰቦቿ ከተቀበለቻት በኋላ ከራሷ ልጆች ጋር ትኖር እንደነበር የከተማ አስተዳዳሩ ኮሚኒኬሽን ባለሙያ አ/ቶ የሱፍ አህመድ ለብስራት ራዲዮና ቴሌቪዥን ተናግረዋል ።

ነገር ግን ግለሰቧ አትታዘዝምና ትሰርቃለች በሚል ግፍና ጭካኔ በተሞላበት መልኩ ልጅቷን በተደጋጋሚ በመደብደብና በመግረፍ በህፃኗ አካል ላይ ከባድ ጉዳት እያደረሰችባት መቆየቷ ተገልጿል ። በዚህም መሠረት ከአከባቢው ነዋሪዎች ለፖሊስ በተደረገ ጥቆማ አማካኝነት ግለሰቧ በቁጥጥር ስር እንደዋለች ተነግሯል ።

የወንጀል ድርጊቱን የፈፀመችው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ውላ ስትጠየቅ ድርጊቱን መፈፀሟንና ያቀረበችው ምክንያት አትታዘዘኝ እንዲሁም የተቀመጠ እቃ ትሰርቃለች ስትል ቃሏን እንደሰጠች ተገልጿል ።

በአበረ ስሜነህ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *