መደበኛ ያልሆነ

ህዳር 28፤2016 –በጂንካ ከተማ በተለያዩ አካባቢዎች ከህዳር 30 ጀምሮ ባሉት ቀናት ከፍተኛ የሆነ የጎርፍ አደጋ ስጋት መኖሩ ተገለፀ

በጂንካ ከተማ አስተዳደር በተለያዩ  አካባቢዎች ከህዳር 30 ጀምሮ  ከፍተኛ የሆነ ዝናብ እንደሚጥል እና ለአካባቢው ነዋሪዎች ስጋት መደቀኑ ተገልጻል። የቅድመ መከላከል ስራ ሊሰራ እንደሚገባ መገለጹን የጂንካ ከተማ አስተዳደር  የኮሙኒኬሽ ባለሙያ አቶ የሱፍ አህመድ በተለይ ለብስራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡

በአካባቢው በ2014 እና በ2015 ዓመት  በተመሳሳይ ወቅትን ሳይጠበቅ በጣለ ከፍተኛ ዝናብ   በተከሰተ ጎርፍ በንብረት ላይ ጉዳት አድርሶ የነበረ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡ በተመሳሳይ  በ2016  ዓ.ም  በተወሰኑ ወረዳዎች ላይ የጎርፍ ጉዳት እየተከሰተ መሆኑን እና ከህዳር 30 ጀምሮ መጠኑን ከፍተኛ የሆነ ዝናብ እንደሚጥል ተነግሯል፡፡ አደጋዎቹ ከተከሰቱባቸው ወረዳዎች መካከልም  በጨርቀቃ ቀበሌ እና በኤርቦሬ ጎንደሮባ ቀበሌ ኮረንታት መንደር በጎርፍ አደጋ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡

አደጋው በሰብል የተሸፈኑ የእርሻ መሬቶችን፤ የአገልግሎት መስጫ ተቋማትን፤ በእርሻ ቦታ ተሰብስበው የተከመሩ ሰብሎችን፣ የግለሰብ መኖሪያ ቤቶች እና የሀይማኖት ተቋማትን በውሃ ሸፍነው ነበር ፡፡

በሌላ በኩል የኦሞ ወንዝ ከመጠን በላይ ሞልቶ  በመፍሰሱ በዳሰነች ወረዳ ከሚገኙ 40 ቀበሊያት ዉስጥ 34 ቀበሌዎችን አጥለቅልቋል። አደጋው ከ17 ሺህ በላይ ሰዎችን ማፈናቀሉ ተገልጿል ።  በወረዳዉ የሚገኙ 21 ደሴቶች ዉስጥ የሚኖሩ የቤተሰብ አባላትና ከአንድ ሚሊዮን በላይ እንስሳቶች በውሃ ሙላት ተከበው የነበረ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በመሆኑም የአካባቢው ነዋሪዎች   ከህዳር 30 በፊት የቅድመ መከላከል ስራ እና  በቆሻሻ  የተደፈኑ ቦዮች  የማስከፈት ስራ ላይ ትኩረት ተሰጥቶት ሊሰራ የሚገባው ጉዳይ እንደሆነ አቶ የሱፍ አህመድ ጨምረው ለብሰራት ሬዲዮ እና ቴሌቪዥን ተናግረዋል፡፡

በምህረት ታደሰ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *