መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 10፤2016 –የደቡብ ኮርያ ተማሪዎች በፈተና ወቅት ለመፈተኛ ከተሰጣቸው ሰዓት 90 ሰከንድ ቀደም ብሎ ፈተናውን ተጠናቋል በሚል በመደወሉ መንግስትን ከሰሱ

የደቡብ ኮሪያ ተማሪዎች የኮሌጅ መግቢያ ፈተና ከታቀደለት ሰዓት በ90 ሰከንድ ቀደም ብሎ በመጠናቀቁ መንግስትን እየከሰሱ ይገኛል።

እያንዳንዳቸው ተማሪዎች 20 ሚሊዮን ዎን ወይም 15,400 የአሜሪካን ዶላር ካሳ ጠይቀዋል። ፈተናውን እንደገና ለመውሰድ የአንድ አመት የጥናት ወጪ ያስወጣናል ሲሉ ተናግረዋል። ስህተቱ በቀሩት ተማሪዎች ፈተና ላይ ተፅዕኖ አሳድሯል ሲል የተማሪዎቹ ጠበቃ ተናግሯል።

ሱኔንግ በመባል የሚታወቀው የሀገሪቱ የኮሌጅ መግቢያ ፈተና ስምንት ሰዓታት የሚፈጅ የፈረና ማራቶን ሲሆን በርካታ የትምህርት ዓይነቶች ይቀርቡ። ሲኔንግ በዓለም ላይ ካሉት በጣም ከባድ ፈተናዎች መካከል አንዱ ነው።የዘንድሮው የፈተና ውጤት ታህሳስ 8 ቀን ተለቋል። ማክሰኞ እለት ቢያንስ በ39 ተማሪዎች የቀረበው ክስ በኮሪያ ዋና ከተማዋ ሴኡል በፈተና ቦታ ላይ ደወሉ ቀድሞ ተደውሏል ሲል ክሱ ያስረዳል።

አንዳንድ ተማሪዎች ወዲያውኑ ተቃውሟቸውን ያሰሙ ቢሆንም ተቆጣጣሪዎቹ ግን የፈተና ወረቀታቸውን እንደወሰዱ ተናግረዋል። መምህራኑ የሚቀጥለው ክፍለ ጊዜ ከመጀመሩ በፊት ስህተቱን ተገንዝበው አንድ ደቂቃ ተኩል በምሳ ዕረፍት ጊዜ መልሰው እንዲፍተኑ አድርገዋል። በወረቀታቸው ላይ የቀሩትን ባዶ ቦታ ብቻ ምልክት ማድረግ እንጂ ምንም አይነት መልሶች እንዲቀይሩ አልተፈቀደላቸውም ።

ተማሪዎቹ በጣም ከመናደዳቸው የተነሳ በቀሪው ፈተና ላይ ማተኮር እንዳልቻሉ ዮንሃፕ የዜና ወኪል ዘግቧል። አንዳንዶቹ ተስፋ ቆርጠው ወደ ቤታቸው ተመልሰዋል። ጠበቃቸው ኪም ዎ-ሱክ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት የትምህርት ባለስልጣናት ይቅርታ አልጠየቁም ብለዋል። የፈተና ማዕከሉን የሚመራው ሱፐርቫይዘር ሰዓቱን በተሳሳተ መንገድ እንደቆጠረ ተመላክቷል።

በደቡብ ኮርያ ተማሪዎች በፈተና ላይ ደወል ቀድሞ በመደውሉ ክስ ሲመሰርቱ ይህ የመጀመሪያው አይደለም። በሚያዝያ ወር በሴኡል የሚገኝ ፍርድ ቤት በ2021 የሱኔንግ ፈተና ወቅት ለፈተናው ከተሰጠው ሰዓት ሁለት ደቂቃ ቀድሞ በመደወሉ ለተማሪዎች ካሳ 7 ሚሊየን ዎን ወይም 5,250 የአሜሪካን ዶላር ካሳ ፈቅዷል።

ከደቡብ ኮርያ ውጪ ደግሞ እ.ኤ.አ. በ 2012 በቻይና ሁናማ ግዛት ውስጥ በሚገኝ ትምህርት ቤት ብሔራዊ የኮሌጅ መግቢያ ፈተና ላይ አራት ደቂቃ ከ48 ሰከንድ ቀደም ብሎ የደወለው የፈተና ተቆጣጣሪ የአንድ አመት የስረ እገዳ ተላልፎበት ነበር።

በስምኦን ደረጄ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *