መደበኛ ያልሆነ

ታህሳስ 18፤2016 – በአዲስ አበባ ከተማ የተማሪዎች ምገባ አገልግሎት ከተጀመረ ወዲህ ትምህርት የሚያቋርጡ ተማሪዎች ቁጥር መቀነሱ ተነገረ

በአዲስ አበባ ከተማ እና ዙሪያዉ በሚገኙ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የምገባ አገልግሎት ከተጀመረ ወዲህ ከትምህርት ገበታቸው የሚቀሩና ትምህርታቸውን የሚያቋርጡ ተማሪዎች ቁጥር መቀነሱን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምገባ  ኤጀንሲ አስታወቀ።

በኤጀንሲው የምገባ አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ስንታየሁ ማሞ ለብስራት ሬድዮ እና ቴሌቪዥን እንደገለጹት በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባና ዙሪያው በሚገኙ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ከ779ሺህ በላይ ተማሪዎች የምገባ አገልግሎትን እያገኙ ይገኛሉ።የአገልግሎቱ ተጠቃሚ ተማሪዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን ገልፀዉ  አገልግሎቱ  በተጀመረበት በ2013 ዓመት 375 ሺህ ተማሪዎች  የምገባ አገልግሎት ማግኘታቸውን አስታውሰዋል።

በቂ ምግብ  መመገብ ያልቻሉ  እና በተለያየ  ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ውስጥ ያሉ ዜጎችን በመመገብ ስራ በአሁኑ ወቅት ከ 7 መቶ ሺህ በላይ ተማሪዎች ቁርስና ምሳ እየተመገቡ ናቸው ሲሉ ምክትል ዋና ዳይሬክተሯ   ጨምረዉ ገልፀዋል ።የተማሪዎች የመማር ብቃት የሚመጣው በተለያዩ ደጋፊ ነገሮች ነው በማለት በምግብ እጦት ሳቢያ በርካታ ተማሪዎች በአዲስ አበባ ከተማ ትምህርታቸውን  ያቋርጣ ነበር ብለዋል፡፡

በቂ ምግብ ያለማግኘት፣ ክፍሉ ውስጥ የመውደቅ ፣ንቁ ሆነው ያለመማር እና የተለያዩ ችግሮች በትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚስተዋሉ መሆናቸውን አንስተው በምገባ ፕሮግራሙ ይህን መቅረፍ ተችሏል፡፡በቀጣይም በምገባ አገልግሎት ውስጥ ለተማሪዎች የሚቀርቡ የምግብ ዝርዝር ዓይነቶችን የማሻሻል ስራዎች እንደሚሰሩ  ወ/ሮ ስንታየሁ ጨምረዉ ለጣቢያችን ተናግረዋል፡፡

በቅድስት ደጀኔ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *